አገራዊ ለውጡ ለተፈጥሮ ሃብት ልማት በሰጠው ትኩረት መሰረት ሀዋሳ ከተማ ከቱሪዝም ሃብቷ የመጠቀም እድሏ ጨምሯል

193

ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) አገራዊ ለውጡ ለተፈጥሮ ሃብት ልማት በሰጠው ትኩረት መሰረት ሀዋሳ ከተማ ከቱሪዝም ሃብቷ የመጠቀም እድሏ መስፋቱን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተናገሩ።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአዲስ አበባም ይሁን በክልሎች የቱሪዝም መስህቦችንና የተፈጥሮ ሃብቶችን በማልማት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለማራመድ እንደሚቻል ተስፋ የሰነቁ ሆነዋል።

የተፈጥሮ ሃብትን በማልማት በተለይም በሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ የተከናወነው ስራ ትልቅ ትምህርት የተገኘበት መሆኑ ይታመናል።

የአንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ የወዳጅነት አደባባይና የሌሎችም ፕሮጀክቶች ክንውን የአመራር ብቃትና ጠንካራ የስራ ባህል የታየባቸው ናቸው።

ከዚህ የልማት ተሞክሮ ልምድ በመቀመር በተለይም የክልል ከተሞች የቱሪዝም መስህቦችንና የተፈጥሮ ሃብታቸውን በማልማት ላይ ይገኛሉ።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ሀዋሳ የታቦር ተራራንና የፍቅር ሃይቅን አልምታ ለቱሪዝም ክፍት ለማድረግ በመስራት ላይ መሆኗን ገልጸዋል።

ከዛሬ 65 ዓመት በፊት የተመሰረተችው ሀዋሳ ከተማ የበርካታ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ብትሆንም አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ምቹ አጋጣሚዎች ሳይፈጠሩላት ዘመናት ተሻግረዋል ብለዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን መንግስት ለእውነተኛ ልማት በሰጠው ትኩረት ሀዋሳ ሀብቷን ለመጠቀም እየሰራች መሆኑን ከንቲባው ይናገራሉ።

ከተማዋን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ፣ ተስማሚና ተመራጭ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
አሁን ላይ በተለይም የታቦር ተራራንና የፍቅር ሃይቅን በማልማት ለቱሪዝም ክፍት ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን ውቢቷን ሀዋሳ የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድርግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ሀዋሳ የህብረ ብሄር አምባ በመሆን እያገለገለች ያለች ደማቅና ድንቅ የፍቅር መገለጫ ከተማ መሆኗን የገለጹት ከንቲባው የጎብኝዎችን ቀልብ በመግዛት የቱሪዝም መናገሻ የማድረጉ ተግባር በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የሀዋሳ ከተማ ሰላምና ጸጥታ በአስተማማኝነቱ እንዲቀጥል፤ በጽዱና አረንጓዴነቷ ምሳሌ ሆና እንድትጠራ የነዋሪው ተሳትፎና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀዋሳ መንገድ ላይ ቆሻሻ መጣል እንደማይገባ ግንዛቤ በመያዝ መንገዶችን በማስዋብና የተተከሉ ዛፍና አበቦችን በመንከባከብ በማህበረሰቡ እየታየ ያለውን ተነሳሽነት ከንቲባው አድንቀዋል።

በተያዘው ዓመት በሀዋሳ ከተማ ከ71 ሺህ ካሬ መሬት ላይ የአረንጓዴ ልማት በህብረተሰብ ተሳትፎ የተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም