መጤ አረምን ወደ ባዮማስ ኃይል የመቀየር ፕሮጀክት ዘላቂ እንዲሆን የግል ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ተጠየቀ

191

ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ)መጤ አረምን ወደ ባዮማስ ኃይል የመቀየር ፕሮጀክት ዘላቂ እንዲሆን የግል ባለሃብቶች ተሳትፎ እንዲያደርጉ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጠየቀ።

በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች መጤ አረም ወይም ፕሮሶፊስ ጁሊፌራን ወደ ባዮማስ ቀይሮ እንደ አማራጭ ኃይል መጠቀም የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል።

ፕሮጀክቱ በሙከራ ደረጃ በአፋር ክልል በአሚባራ ወረዳ በ2 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረ ሲሆን በሥነ- ሥርዓቱ ላይ የፌደራልና የክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ፕሮጀክቱ በክልሎቹ እየተስፋፋ የመጣውን መጤ አረም በዘመናዊ መሳሪያ በማጨድ፣በመፍጨትና በማቃጠል የሚመነጨውን ኃይል ኢንዱስትሪዎች እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው።

ከዚህ ባለፈም ከአረሙ የጸዳውን መሬት ለእርሻ፣ለግጦሽ እንዲሁም ወደ ምርት እንዲመለስ የማድረግ ዓላማ አለው።

ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ላለፉት ዓመታት ቅድመ-ዝግጅት የተደረገ ሲሆን፤የአውሮፓ ህብረት አረሙን መሰብሰቢያ መሳሪያ ግዥና ለጥናት የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።

ከአረሙ ነጻ የሆነውን መሬት ወደ ምርታማነት ቀይሮ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ግብርና ሚኒስቴር፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴርን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ስምምነት ፈርመዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ "የትላንትና የዛሬ ችግሮች እውቀትና ጥበብ ከጨመርንባቸው የነገ ዕድልና መልካም አጋጣሚዎች እንደሆኑ ፕሮጀክቱ አመላካች ነው" ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የእርሻ መሬት ለምነቱ እንዲመለስ፣ ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር፣ሙቀት አማቂ ጋዝ የሚያመነጩ የኃይል አማራጮችን ለመቀነስ ያለው ፋይዳም ከፍ ያለ መሆኑን አብራርተዋል።

አሁን ላይ አረሙን ለመሰብሰብ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ መሳሪያዎች በአማካይ በቀን 8 ሄክታር መሬት ብቻ እየሸፈኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ባሉት ጥቂት መሳሪያዎች አረሙን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ አዳጋች መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ የግል ባለሃብቱም ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ባለሃብቶች ከአረሙ በጸዳው መሬት ላይ በእርሻ ሥራዎች ላይ ከመሳተፍ ባሻገር ለኢንዱስትሪዎች ኃይል ማቅረብ ላይ መሳተፍ የሚችሉበት ዕድል መኖሩን አብራርተዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አወል አርባ፤ አረሙ የልማት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ጠቁመው፤ለችግሩ መፍትሔ የሚሆን ፕሮጀክት መምጣቱ ለሕዝባችን ትልቅ ብስራት ነው ብለዋል።

የኬሚካል እና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ምርምር ማዕከል የአካባቢ ጥበቃ ሙያ ደህንነትና ኢነርጂ ዳይሬክተር ዳዊት ዓለሙ በበኩላቸው፤ አረሙን በማቃጠል ከሚገኘው ኃይል ፋብሪካዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ፋብሪካዎች ለሚጠቀሙት ድንጋይ ከሰል ግብዓት ከ300 እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደምታደርግ አስታውሰው፤ፕሮጀክቱ ወጪውን ለማዳን ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአፋር ክልል አሚባራ ወረዳ ነዋሪዎች በመጤ አረሙ ሳቢያ ብዙ ችግር አሳልፈናል፤የፕሮጀክቱ መምጣቱ ትልቅ ተስፋ ሰጥቶናል ብለዋል።በሳይንሳዊ መጠሪያው ፕሮሶፊስ ጁሊፌራ በሚል የሚታወቀው መጤ አረም በአፋርና ሶማሌ ክልሎች በ2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ተስፋፍቶ ይገኛል።

አረሙ በአሁኑ ወቅት ወደ ኦሮሚያ፣ደቡብና አማራ ክልሎች በመስፋፋት ላይ ሲሆን አሁን ያለው የአረም መጠን ለሚቀጥሉት 50 ዓመታት የባዮማስ ኃይል መስጠት እንደሚችል ተገምቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም