የአረንጓዴ አሻራ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን እቅድ ለማሳካት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል

193

ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአረንጓዴ አሻራ የሚተከሉ የፍራፍሬ ችግኞች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን እቅድ ለማሳካት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የጉለሌ እጽዋት ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ በላይ ገለጹ።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የአረንጓዴ ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ እየሰራች ነው።

ይህን ለማሳካትም በ2011 ዓ.ም  የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ  የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ዘንድሮ አራተኛ ዙር ላይ ደርሷል።

የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ከሚተከሉት ውስጥ 52 በመቶዎቹ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የራሳቸው ሚና ያላቸው ችግኞች መሆናቸው ተገልጿል።

በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ በላይ፤ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናውም ጭምር የአየር ንብረት ለውጥ መሻሻል ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩ በብዛት እየተተከሉ ያሉት የፍራፍሬ ተክሎች መሆናቸውን አስታውሰው፤ በዘንድሮው ንቅናቄም ይህንኑ ማስቀጠል ይገባል  ነው ያሉት።

ይህም የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የአረንጓዴ ኢኮኖሚን እውን በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል እንደሚያስችል በማንሳት።

ዶክተር ብርሃኑ እንደሚሉት በኢትዮጵያ  ለመድኃኒትነትና ሌሎችም አገልግሎቶች የሚውሉ ከ6 ሺህ በላይ የእጽዋት ዓይነቶች ቢኖሩም እየጠፉና እየተመናመኑ በመሆኑ ሀገር በቀል እጽዋቱን የማልማት ሥራም በልዩ ትኩረት  መከናወን አለበት።

አረንጓዴ አሻራ ከአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ባሻገር የሃብት ምንጭና የሥራ እድል መፍጠሪያ በመሆኑ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ተመራማሪው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ዜጎችና ተቋማት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የሚያደርጉት ተሳትፎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሻሻለ ቢመጣም የችግኝ አተካከሉ ላይ የጥንቃቄ መጓደል እንደሚስተዋል አንስተዋል።

ይህ ደግሞ የችግኞችን  የፅድቀት ምጣኔ እንደሚቀንስ የገለጹት ዶክተር ብርሃኑ፤ በተለይ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች አተካከል ላይ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል።

ለችግኝ ተከላ የሚደረገው ጥንቃቄም በእንክብካቤ ሂደት መቀጠል እንዳለበት በመጥቀስ፤ በአረንጓዴ አሻራ የታለመውን ግብ ለማሳካትም ሙያዊ እገዛን ማጠናከር እንደሚገባም ነው ያብራሩት።

ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶችን በማደራጀት ችግኞችን በባለቤትነት እንዲንከባከቡ በማድረግ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ሊፈጠርላቸው እንደሚገባም እንዲሁ።

ዶክተር ብርሃኑ አክለውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተስማሚ የአየር ንብረት ያላቸው ሀገራት ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ተመራጭ መሆናቸውን ገልጸው፤ በኢትዮጵያም የአረንጓዴ አሻራን በማጠናከር ለዘርፉ ምቹና ሳቢ ሁኔታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሮች 18 ቢሊየን የሚጠጉ ችግኞች መተከላቸውን መንግሥት ገልጿል።

ዘንድሮ አራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር  የተጀመረ ሲሆን 6 ቢሊየን ችግኞች እንዲተከሉ ግብ ተይዟል።

የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን ሰኔ 14 ቀን የአራተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ሲጀመር እንዳሉት፤ ከሦስት ዓመት በፊት ከተተከሉ የፍራፍሬ ችግኞች ውጤት መገኘት ጀምሯል።

በዚህም አቮካዶና መሰል ፍራፍሬዎችን ወደ ውጪ በመላክ 82 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው፤ ለዘንድሮው የችግኝ ተከላም 500 ሚሊዮን የአቮካዶ ችግኞች መዘጋጀታቸውንም ጠቅሰዋል።

ማንጎና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸውን የተናገሩት አቶ ኡመር፤ በችግኝ ጣቢያዎች በየዓመቱ ከ184 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ እድል እየተፈጠረላቸው ነው ብለዋል።