አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በፖለቲካው መስክ የተጀመሩ አካታች አካሄዶች ዜጎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲሰለፉ እድል የፈጠሩ ናቸው

632

ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በፖለቲካው መስክ የተጀመሩ አካታች አካሄዶች ዜጎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲሰለፉ እድል የፈጠሩ መሆናቸውን የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባላት ተናገሩ፡፡

ከኀብረተሰቡ የሚነሱ የሰላምና ደህንነት ጥያቄዎችን በመመለስ ጠንካራና የተረጋጋች አገር ለመገንባት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያ ተለዋዋጭ በሆኑ ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እያለፈች ሲሆን፤ በዚህም ኢትዮጵያዊያን እንደ አገር ታላላቅ ፈተናዎችን ተጋፍጠው አልፈዋል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባላት እንደሚሉት፤ ባለፉት አራት ዓመታት በተለይ በፖለቲካው መስክ አሳታፊ ምህዳር ለመፍጠር የተከናወኑ ተግባራት እንደ አገር በርካታ እድሎችን የፈጠሩ ናቸው፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስትርና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሙፈሪያት ካሚል፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ ምእራፍ የከፈቱ አካሄዶች ተግባራዊ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

ይህም በኢትዮጵያ ስር ሰዶ የቆየውን የመጠላለፍና የመጠፋፋት የፖለቲካ አካሄድ እንዲቀየር ከማድረጉ በላይ ገዥና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ አገር እንዲመሩ ያደረገ ነው ይላሉ፡፡

ለውጡን የሚመራው መንግስት የቆዩ የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱንም ነው የተናገሩት፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ኃላፊና የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጸጋዬ ማሞ በበኩላቸው ገዥው ፓርቲ ብልጽግና የኢትዮጵያ ፖለቲካ መገለጫ የነበረውን "የጠላትና ወዳጅ" አካሄድ በአጭር ጊዜ ወደ አካታች ምህዳር መቀየር መቻሉን ይገልጻሉ፡፡

May be an image of 1 person and suit

ይህም ዜጎች በአገር ጉዳይ በእኔነት መንፈስ በጋራ እንዲሰለፉ ማድረጉን ነው ያብራሩት፡፡

የሽግግር ሂደት ጊዜን የሚጠይቅና በፈተና የሚያልፍ መሆኑን የጠቀሱት ስራ አስፈጻሚዎቹ፤ ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ ስኬቶች ቢመዘገቡም አገርን የፈተኑ አደጋዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በተለይ በፖለቲካ ምህዳሩ ላይ የተፈጠረውን ነጻነት በአግባቡ ካለመጠቀም ጋር ተያይዞ በህዝብና አገር ላይ አደጋ የሚፈጥሩ አካላት እየተበራከቱ መምጣታቸውን አንስተዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ኀብረተሰቡ የህግ የበላይነት እንዲከበር በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያነሳ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም መንግስት ወቅታዊ አገራዊ ፈተናዎችን በመገምገም የአገርና ህዝብ ድህንነትን ለማስጠበቅ አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግስት እያከናወነ ለሚገኘው ህግ የማስከበር ስራ ኀብረተሰቡ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ማስቀመጡን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም