የህግ ታራሚዋን አስገድዶ የደፈረው ፖሊስ በዘጠኝ ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

172

ጭሮ፣ ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የህግ ታራሚዋን በመድፈር የተከሰሰው ፖሊስ በዘጠኝ ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወሰነ።

ትናንት ከሰዓት በኋላ 9፡00 ሰዓት ላይ በዋለው ችሎት ረዳት ሳጅን ሰብስቤ ሙሉጌታ አባተ የተባለው ፖሊስ በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡

ፖሊሱ በምርመራ ሰበብ የህግ ታራሚዋን መድፈሩ በምስክሮችና በህክምና ማስረጃ በመረጋገጡ በዘጠኝ አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል፡፡

በችሎቱ የተሰየሙት ዳኛ ኤልሳቤት ታደሰ እንደገለጹት፤ ድርጊቱ የተፈፀመው በምእራብ ሀረርጌ ዞን ሸነን ኡጎ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ነው፡፡

በግንቦት 14 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ላይ የግል ተበዳይ የሆነችው የህግ ታራሚ እመረምርሻለሁ በሚል ሰበብ ወደ አዳራሽ በመጥራት ከፍተኛ ድብደባ ካደረሰባት በኋላ አስገድዶ ደፍሯታል፡፡

የግል ተበዳይ ወደ መሰላ ማረፊያ ቤት በተዘዋወረችበት ወቅት በሰጠችው ቃልም ፖሊሱ ይህን ጉዳይ ለሰው ብትናገሪ ለኔ ከጥፍሬ በታች ነሽ በማለት ያስፈራራት መሆኑንና ከፍተኛ ጥቃት ያደረሰባት መሆኑን ተናግራለች፡፡

ድርጊቱ በተፈጸመ እለት ምሽት በስፍራው ከነበሩ ሶስት ሰዎች እንዲሁም በማግስቱ ምግብ ቤት ጓደኞቹን አግኝቶ እንብላ ሲሉት አይ ከእናተ ጋር አልበላም ሴት ደፍሬ ነው የመጣሁት ብሎ ሰው በተሰበሰበበት መናገሩን መስክረውበታል፡፡

በሰዎች ምስክር ማስረጃና ከጭሮ አጠቃላይ ሆስፒታል በተገኘ መደፈሯን በሚያረጋግጥ የህክምና ማስረጃ ጥፋኛ ሆኖ በመገኘቱ በዘጠኝ ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ወስኖበታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም