አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎ ከምክር ቤት አባላት የተወጣጡ ሁለት ቡድኖችን በማቋቋም ስምሪት ሰጡ

97

ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎ ከምክር ቤት አባላት የተወጣጡ፣ ወቅታዊ ጉዳዮችን የሚያጣሩ ሁለት ቡድኖችን በማቋቋም ስምሪት ሰጥተዋል፡፡

አፈ ጉባኤው ለጤና፣ ማህበራዊ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጻፉት ደብዳቤ “ሰሞኑን በጋምቤላ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ውስጥ በተወሰኑ አካባቢዎች በአሸባሪውና ተላላኪው ሸኔ በንጹሃን ዜጎች ላይ እጅግ አሰቃቂ፣ አሳዛኝና በሰው ልጆች ላይ መፈጸም የሌለበት ግፍ ተፈጽሟል” ብለዋል።

በመሆኑም ሂደቱን ማጣራትና ተገቢውን ድጋፍ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ምክር ቤቱ እንደሚያምን ገልጸዋል።

የደረሰውን ጉዳት መጠንና የሚያስፈልገውን አስቸኳይ ድጋፍ በቋሚ ኮሚቴው በኩል ተጣርቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ የሰጡት አፈ ጉባኤው፤ የሚቀርበውን የጉዳት መጠን መረጃ መነሻ በማድረግ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ተከታትሎ አስፈላጊውን ድጋፍ በአስቸኳይ ለዜጎች እንዲያቀርብ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም በሂደቱ የታየውን ከሰብዓዊ መብት ጋር የሚያያዙ ጉዳዮችን አጣርቶ ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም