ህብረቱ ትውልድን በማነጽና በመቅረጽ መትጋት ይኖርበታል - ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ

117
አዲስ አበባ መስከረም 1/2011 የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያን ህብረት ትውልድን የማነጽና የመቅረጽ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አሳሰቡ። በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የለውጥ ሂደት ዘላቂ  ሆኖ ይቀጥል ዘንድ ህዝቡ ከጅምላ ፍረጃ፣ ጥላቻ እና የጠባብነት ስሜት እንዲቆጠብ ጥሪ ቀርቧል። የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያን ህብረት የዘመን መለወጫ በዓልን በርከታ ተከታዮቹ በተገኙበት በተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶች በአዲስ አበባ ስታዲየም በዛሬው እለት  አክብሯል። በበዓሉ ላይ የታደሙት ምክትል ከንቲባው ኢንጂነር ታከለ እንደተናገሩት፤ ህብረቱ ብዙ ኃላፊነት እንዳለበት በመቀበል ትውልድን በመልካም ተግባር በማነጽና በመቅረጽ ረገድ መትጋት አለበት። ህብረቱ ህዝቡ ደግ ፣ የዋህ ፣ ቅን ልቦና ያለውና ከራሱ ቀንሶ ለሌሎች የሚሰጥ መሆኑን ተገንዝቦ መንፈሳዊ ህይወቱን ከሚያበላሹ ተግባራት ሊጠበቅ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል። "ስለሆነም መረን የወጣ ግለሰብ በአባታዊና ሃይማኖታዊ ምክር መመለስ አለበት" ሲሉም  ምክትል ከንቲባው አሳስበዋል። ምክትል ከንቲባው አክለውም "ዘመናትን በራሱ ጥበብ የሚያቀዳጅ ፈጣሪ፤ አገሪቷንና ከተማዋን ከአደገኛ የጥፋት ማዕበል አትርፎ ወደ አስደማሚ ምዕራፍ፣ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲሁም ፍቅርና ብርሃን ወደበራበት 2011 ዓ ም በሰላም አድርሷታል" በማለትም ገልፀዋል። በአዲሱ ዓመት ህብረቱ ከከተማ አስተዳዳሩ ጋር ለሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ አረጋግጠዋል። የህብረቱ ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶ በበኩላቸው የአገር ሰላም ተጠብቆ በአንድነትና በፍቅር ተከባብሮ ለመኖር ይቅርታ፣ ምህረትና ፍቅር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሁሉም መገንዘብ እንዳለበት ገልጸዋል። "ፍቅር በሚሰበክበት ዘመን ጥላቻን በማስፋፋት፣ እርቅ እየታወጀ በቀልን በመስበክ፣ አንድነት እየተበሰረ የሚለያዩ ቁስሎችን በመጎርጎር ትውልድንና አገርን መታደግ አይቻልም" ሲሉም ፓስተር ፃድቅ መክረዋል። ''ፍቅርን ከቃል ባለፈ በተግባር የሚገለጥ፣ ይቅርታችን የበቀልን ቁስል የሚሽርና የበደል ስሜትን የሚጥል ሊሆን ይገባል'' ሲሉ ተናግረዋል። ሃይማኖታዊና ማህበራዊ ግንኙነቶችን የሚያጎለብቱ እንደዚሁም የፖለቲካ አስተሳሰቦችን የሚያጠነክሩ ተግባራትን በማከናወን የእርስ በርስ መተባበርን ፣ መከባበርንና ወንድማማችነት ያለውን መንፈስ ማጎልበት ተገቢ እንደሆነ አስገንዝበዋል። አሁን የተፈጠረው የአንድነትና ሰላም ለውጥ ዘላቂ  ሆኖ ይቀጥል ዘንድ ከማንኛውም ዓይነት የጅምላ ፍረጃና ጥላቻ እንዲሁም የጠባብነት ቃልና ተግባር ህዝቡ እንዲቆጠብ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም