የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን “ጎጆ ለማውጣት” ሁላችንም በቻልነው ሁሉ መደገፍ አለብን

162

ሰኔ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን “ጎጆ ለማውጣት” ሁላችንም በቻልነው ሁሉ መደገፍ አለብን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

የፌዴሬሽኑ 11ኛ ክልል ሆኖ የተመሰረተውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ለማጠናከር ያለመ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ክልሉ ሲደራጅ በርካታ ነገሮች የሚያስፈልጉት በመሆኑ እገዛ ይሻል ብለዋል።

በአገር ወግና ባህል አዲስ የሚቋቋምን “ጎጆ ማውጣት” የተለመደ በመሆኑ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ጎጆ በማውጣት ሁላችንም እንደግፈው በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን የበርካታ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት በመሆኑ ባለሃብቶች ኢንቨስት ቢያደርጉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በመግለጽ በክልሉ እንዲያለሙ ጠይቀዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኢንጀነር ነጋሽ ዋጌሾ የገቢ ማሰባሰቢያው ክልሉን በብዙ መልኩ ለማደራጀትና ለማጠናከር እንደሚረዳው ገልጸው፤ መላው ኢትዮጵያዊያን ከተመሰረተ ስምንት ወራት ያስቆጠረውን ክልል በሚችሉት ሁሉ እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብሩ በክልሉ ያሉ በርካታ የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን የማስተዋወቅ ዓላማ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብሩ የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች፤ ባለሀብቶች፣ ዲፕሎማቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ የምዕራቦ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ የዳውሮ ዞን እና የሸካ ዞን እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ ህዝቦች በህዝበ ውሳኔ በአንድ ክልል ለመደራጀት መወሰናቸውን ተከትሎ መመስረቱ ይታወሳል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ