በግቢያችን የጓሮ አትክልትን በማልማት ተጠቃሚ ሆነናል- የአርባ ምንጭ ነዋሪዎች

139

አርባ ምንጭ፤ ሰኔ 15/2014 (ኢዜአ) በግቢያቸው የጓሮ አትክልትን በማልማት የዋጋ ንረት ከመቋቋም ባለፈ ወጪያቸውን በመቀጠብ ተጠቃሚ መሆናቸውን በአርባ ምንጭ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

በከተማ ግብርና 1ሺህ 848 ሰዎች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙና ከእነዚህም የወጣቶችና የሴቶች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን የከተማው አስተዳደር የግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል  ወይዘሮ ከበቡሽ ካንኮ እንደገለጹት፤ በግቢያቸው ውስጥ የተለያዩ ዕቃዎችን በመጠቀም የጓሮ አትክልት እያለሙ ነው፡፡

ወይዘሮ ከበቡሽ ከጓሮ አትክልት በተጨማሪም በሶብላ፣እንስላል፣ጤና አዳም፣ድምብላል፣ዝንጅብል፣ የስጋ መጥበሻ(ሮዝመሪ) በግቢያቸው ያለማሉ።

ለጥላና ለምግብነት አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ሽፈራውና ፓፓያ የመሳሰሉ አትክልት በግቢያቸው ባለው አነስተኛ ማሳ በማልማት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

”የጓሮ አትክልት የማያለሙ ሰዎች ከገበያ በውድ ዋጋ ለመግዛትና ለትራንስፖርት ወጪ ሲዳረጉ እኔ ግን እነዚያን ከግቢዬ የማገኝ በመሆኔ ለገበያ ላይ ወጪ አልገደድም” ብለዋል፡፡

የልዩነህ ዱባለ አካዳሚ ባለቤት አቶ ልዩነህ ዱባለ በትምህርት ቤታቸው ግቢ የጓሮ አትክልት ልማትን ለተማሪዎች ግንዛቤ ለመፍጠርና በየቤታቸው መጠቀም እንዲችሉ በተግባር በተደገፈ መንገድ እንደሚያስተምሩ ነው የገለጹት።

በዚህም ቀይ ስር፣ሰላጣ፣ ቲማቲም፣ ካሮት፣ ጎመን፣ ቆስጣና ሌሎች የጓሮ አትክልትን እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እያንዳንዱ ሰው የጓሮ አትክልትን ቢያለማ ለግዢ የሚያወጣውን ገንዘብ ማዳን እንደሚችል የሚናገሩት አቶ ልዩነህ፤ የከተማ ግብርና በምግብ ራስን ለመቻል ብሎም ገበያን ለማረጋጋት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

በከተማ ግብርና ለማልማት የግድ ሰፋፊ መሬትና ወንዞች ሳያስፈልጉ በጓሯችን በማልማት ተጠቃሚ መሆን እንችላለን ብለዋል አቶ ልዩነህ፡፡

የጓሮ አትክልት ዓመቱን ሙሉ በግቢያቸው ውስጥ ስለሚያለሙ ባለቤታቸው የጓሮ አትክልት ለመሸመት  ገበያ ወጥተው እንደማያውቁ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ሳሊሌ ሻንካ ናቸው፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሳልፋቆ ቢሻው ፤በከተማው በግለሰብ ቤቶች፣ በሆቴሎች፣ በትምህርት ቤቶችና በመንግስት ተቋማት 780 ሄክታር በላይ መሬት በጓሮ አትክልት እየለማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የከተማ ግብርናው ገበያ ለማረጋጋት ድርሻ ስላለው ልማቱ በልዩ ትኩረት  እየተመራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፣

”የከተማ ግብርና ብዙ መሬት አይጠይቅም” ያሉት ሃላፊው፤ ክፍት በሆኑ ቦታዎች፣ በበረንዳ፣ በአጥር ዙሪያ የተለያዩ ዕቃዎችን በመጠቀም ማልማት ይቻላል ነው ያሉት፡፡

ጽህፈት ቤቱ የዘር ፣የስልጠና በሙያ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸውም አስታውቀዋል።

የከተማ ግብርና በቀጣይ እንደ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ሃላፊው አመልክተዋል፡፡

የከተማ ግብርና በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና ዋጋን ለማረጋጋት አንደኛው ስልት ተደርጎ በመተግበር ላይ ነው።