አገር አቀፍ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ኤግዚቢሽንና ባዛር በነገው እለት በአዲስ አበባ ይጀመራል

112

  ሰኔ 15/2014 (ኢዜአ) ከ200 በላይ ኢንተርፕራይዞች የሚሳተፉበት አገር አቀፍ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ኤግዚቢሽንና ባዛር በነገው እለት በአዲስ አበባ የሚጀመር መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ገለጸ።

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከነገ ጀምሮ ለስምንት ተከታታይ ቀናት በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቅጥር ጊቢ ይካሄዳል።

በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ እንጨትና ብረታብረትን ጨምሮ በአምስት ዘርፎች 227 ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች በባዛርና ኢግዚቢሽኑ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ብሩ ወልዴ፤ የነገውን መርሃ ግብር በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ባዛርና ኤግዚቢሽኑ አምራች ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን ለተጠቃሚዎች አቅርበው የሚያስተዋውቁበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንተርፕራይዞች ከምርት ሂደት እስከ ገበያ ያለውን ሂደታቸውንና ምርቶቻቸውን ለተጠቃሚዎች እንዲያስተዋውቁ ይደረጋልም ነው ያሉት።

በ2014 በጀት አመት 11 ወራት በነባርና አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ከ87 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን አስታውሰው በቀጣይም በትኩረት ይሰራበታል ብለዋል።

ኢንተርፕራይዞች ወደ ውጪ ከላኳቸው ምርቶችም 25 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካትም ከ382 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማትረፍ መቻሉን ገልፀዋል።

የአግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች እንደ እርድ፣ እንጀራ፣ ማር፣ ቡናና የመሳሰሉትን ምርቶች በአብዛኛው የተላኩ ምርቶች እንደሆኑም ተናግረዋል።

ለ982 ኢንተርፕራይዞች 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የስራ ማስኬጃ ብድር እንዲሁም ለ1 ሺህ 871 ኢንተርፕራይዞች 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በሊዝ ፋይናንስ ማቅረቡንም ገልጸዋል።

በግብአት፣ በኃይል አቅርቦትና ሌሎች ምክንያቶች ስራ አቁመው የነበሩ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ስራ ለመመለስ ድጋፍ መደረጉንም አብራርተዋል።