ምክር ቤቶቹ የበለስ ስኳር ፋብሪካ ከሙከራ ወደ ተሟላ የማምረት ስራ ለማሸጋገር እናግዛለን አሉ

120

እንጅባራ ፤ ሰኔ 15/2014 (ኢዜአ) የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ከሙከራ ወደ ተሟላ የማምረት ስራ ለመሸጋገር እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያግዙ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደርና የመተከል ዞን ምክር ቤቶች አስታወቁ።

የምክር ቤቶቹ አባላት የስኳር ፋብሪካ  ፕሮጀክቱን እንቅስቃሴ  ጎብኝተዋል።

በዚህ ወቅት የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ አቶ በላይነህ ወንድም ፤ ፋብሪካው ከሙከራ ወደ ተሟላ የማምረት ስራ ለመሸጋገር የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በዚህም ከመተከል ዞን ምክር ቤት ጋር በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የጀመርነውን ትስስር ወደ ልማት ለማሣደግ የሚያስችል የጋራ ዕቅድ ነድፈን እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የሁሉም ኢትዮያውያን ቢሆንም የቅርብ ተጠቃሚው አጎራባች ህዝቦች ስለሆንን ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እንዲያመጣ የሚያስችል ቅንጅት ተፈጥሮ ይሰራል ነው ያሉት።

በተለይም የአካባቢው ሰላም ተጠብቆ ምንም ዓይነት መስተጓጎል ሳይደርስበት በፍጥነት በሙሉ አቅም ማምረት እንዲጀምር ሁለቱም ህዝቦች ፕሮጀክቱን በባለቤትነት እንዲጠብቁም አሳስበዋል።

ሁለቱ ዞኖች በጋራ ኢንቨስትመንትና የገበያ ትስስር እንዲፈጠርም የጋራ ንግድና የልማት ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ስኳር ፋብሪካው በሙሉ አቅም በማምረትም በሃገሪቱ  አሁን ያለውን የገበያ ክፍተት እንዲሞላ አስፈላጊው እገዛ ሁሉ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።

የመተከል ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ጆንሴ ኢቢሳ በበኩላቸው፤ ፋብሪካው በሁለቱ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ መገንባቱ ለኢኮኖሚ ትስስር የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

ፋብሪካው በሃገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠለትን ግብ እንዲያሳካ የአካባቢውን ሰላም እንዲጠበቅ በማድረግ አሁን ካለበት  የሙከራ  ምርት ስራ ወደ ሙሉ ማምረት ለመሸጋገር የሚያደርገውን ጥረት እናግዛለን ብለዋል።

የሁለቱን ህዝብ የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን ለማከናወንም አቻ ምክር ቤቶች በጋራ እየሰራን ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት እንዲገባም ምክር ቤቱና ህዝቦች በባለቤትነት ስሜት በጋራ እንዲጠብቁት የዕቅዳችን ክፍል አንዱ አካል ነው ብለዋል።

”ፋብሪካው እያከናወነ ባለው የሙከራ ምርት ከ4 ሺህ ኩንታል በላይ የስኳር ምርት ማምረት ችሏል” ያሉት ደግሞ የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አበበ ይሁን ናቸው።

ለፋብሪካው ግብዓት በ5 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ  የሸንኮራ አገዳ እየለማ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ወደ ሙሉ ማምረት ሲገባ በቀን 12 ሺህ ኩንታል የማምረት አቅም አለው ብለዋል።

እንደ  ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለፃ፤ ፕሮጀክቱ በ122 ሄክታር መሬት ላይ ሙዝ፣ ብርቱካንና ማንጎ  እያመረተ እንደሚገኝ አመልክተው፤ ከአንድ ሺህ 600 ለሚበልጡ ወገኖችም የስራ እድል መፍጠሩን አስረድተዋል።

በተያዘው ዓመት ብቻ በፕሮጀክቱ አቅራቢያ ለሚገኙ የፈንድቃ፣ ፓዌ እና ግልገል በለስ ከተሞች 128 ሚሊዮን 989 ሺህ ብር ወጭ በማድረግ የመንገድ፣ የመብራትና የመጠጥ ውሃ አገልግሎት እንዲያገኙ መድረጉንም  አብራርተዋል።

የምክር ቤቶቹ አባላት ጉብኝትም የሁለቱን ዞኖች ህዝብ በባለቤትነት እንዲጠብቀውና በየደረጃው ባለው አመራር ትኩረት እንዲያገኝ የማድረግ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ በአማራ ክልል አዊ ዞን ጃዊ ወረዳና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ፓዌ ወረዳ የሚፈሰውን በለስ ወንዝ ተከትሎ በ25 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ፕሮጀክት መሆኑ ተመልክቷል።