የእምነት ተቋማት የአገር ሰላምና የህዝቦችን አብሮነት መጠናከር ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው እንዲሰሩ ተጠየቀ

ሰኔ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የእምነት ተቋማት የአገር ሰላምና የህዝቦችን አብሮነት መጠናከር ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው እንዲሰሩ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች ጠየቁ።

በጉባዔው የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የታደሙበት አገር አቀፍ የሰላም ጉባዔ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ጉባኤው “ሃይማኖት ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደ ሲሆን ለኢትዮጵያ ሰላምና ለህዝቦች ሰላማዊ ህይወት ከምንም በላይ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ መሆኑ ተነስቷል። 

በጉባኤው ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዩ የእምነት አባቶች ሰላም ከሌለ ምንም ነገር ማከናወንና ወጥቶ መግባት የማይቻል በመሆኑ ሁላችንም ለሰላም ቅድሚያ እንስጥ ብለዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ እያታዩ ያሉ ችግሮች አደገኛ አዝማሚያ እየተስተዋለባቸው መሆኑን ጠቅሰው የመፍትሄው አካሎች እኛው ልንሆን ይገባል ነው ያሉት።

በመሆኑም በተለይ የእምነት ተቋማት ለአገር ሰላምና የህዝብ አብሮነት መጠናከር ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው የማስተማር ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሀፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ ማንኛውም ሃይማኖት የፍቅር፣ የአብሮነት፣ የመተባበርና ሰብአዊነትን የሚሰብክ እንጂ የግጭትና ጥላቻ መንስኤ አለመሆኑን ገልጸዋል።

በርካታ አማኝ ባለበት አገር ግጭትና የሰላም እጦት ፈተና እየሆነ መምጣቱ ሁሉንም ሊያሳስብ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የእምነት አባቶች ለኢትዮጵያ ሰላምና ለህዝቦች አብሮነት መጠናከር ያለብንን ድርብ ሃላፊነት በአግባቡ እንወጣ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱአለም፤  ሰላም የሰፈነበት ማህበረሰብ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት በተለይም የእምነት ተቋማት የላቀ ሚና ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ከውይይት ሒደቶች በተጨማሪ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ የሰላምና የእርቅ ስርአትን በመጠቀም ለአገር የሰላም ግንባታ ማዋል እንደሚገባም ተናግረዋል።

የአገርን ሰላምና መረጋጋት በፅኑ መሰረት ላይ ለማኖር በተለይም የሃይማኖት አባቶች እና መሪዎች የማይተካ ሚና እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።

መንግስትም የሰላምና የእርቅ እሴቶችን በመጠቀም ዘላቂ ሰላም ግንባታ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም