ቋሚ ኮሚቴው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለትምህርት ጥራት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳሰበ

114

ሰኔ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለትምህርት ጥራት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት ፤ስራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

የሰው ሃብት ልማት፣ ስራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከትምህርት ስልጠና ባለስልጣን እንዲሁም ከኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርትና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ማህበር አመራሮች እና አባላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

ውይይቱም በዋናነት በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶችና እየገጠሟቸው ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ 

የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በዚሁ ወቅት የትምህርት ጥራት መንግስት በሚያደርገው ጥረት ብቻ እውን ሊሆን እንደማይችል ጠቅሰው፤ የግል የትምህርት ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ተቋማቱ ለትምሀርት ጥራት ትኩረት በመስጠት ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት መስራት አለባቸው ነው ያሉት፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ፍሬው ተስፋዬ በበኩላቸው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቁና ስነ-ምግባር የታነጸ ዜጋ የማፍራት ኃላፊነት እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡

የግል የትምህርት ተቋማትን በማገዝ ረገድ ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ነው የጠቆሙት፡፡

ተቋማቱ  የመረጃ አያያዝ ስርዓታቸውን ማዘመንና ህብረተሰቡን በጥናትና ምርምር መደገፍ እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡

የትምህርት ስልጠና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም አድማሴ፤ ባለስልጣኑ በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ቋሚ ኮሚቴው ይህንን ጥረት በማገዝ ረገድ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መንግስት የግል የትምህርት ተቋማትን በቅርበት በመደገፍና በመከታተል የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት መስራት እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርት እና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ሞላ ፀጋዬ ናቸው፡፡

ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በሰጡት ምላሽ  ቋሚ ኮሚቴው በቀጣይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የግል የትምህርት ተቋማትን ለመደገፍ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም