በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ የመድኃኒታማና መዓዛማ እጽዋቶችን የማላመድና የማስፋት ስራ እየተከናወነ ነው

410

ሀዋሳ፤ ሰኔ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ የመድኃኒታማና መዓዛማ እጽዋቶችን የማላመድና የማስፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

መንግስት ዘርፉን በግብርና ኤክስቴንሽን ውስጥ ቢያካትተው  ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የማስገኘት አቅም እንዳለውም ተመላክቷል።  

በኢንስቲትዩቱ የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል የመድኃኒታማና መዓዛማ እጽዋቶች ምርምር ፕሮግራም ብሄራዊ አስተባባሪና ተመራማሪ አቶ ደስታ ፍቃዱ ለኢዜአ እንደገለጹት ማዕከሉ የመድኃኒታማና መዓዛማ እጽዋት የልህቀት ማእከል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ መዓዛማና መድሃኒታማ እጽዋቶችን ወደ ሀገር ውሰጥ በማስገባትና  በማላመድ  ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ  መሆኑን ጠቁመዋል።

ሀገር በቀል ዝርያዎችንም  ከአርሶ አደር ማሳና ከደኖች ውስጥ በማሰባሳብ ጥናትና ምርምር እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተደረገውእንቅስቃሴ በርካታ ምርት ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት ዝርያዎቹን የማስመዝገብ ስራ እየተከናወነ  መሆኑን አመላክተዋል።

ተመራማሪው እንዳሉት በማእከሉ ካሉ ከ100 በላይ መዓዛማና መድሃኒታማ እጽዋቶች ውሰጥ 33ቱ ዝርያቸው ተመዝገቦ ተጨማሪ ጥናትና ምርምር እየተካሄደባቸው ይገኛል።

በዘርፉ በርካታ ሀገር በቀል ሀብት መኖሩን የጠቀሱት አቶ ደስታ አብዛኞቹ በጫካ ውስጥ የሚገኙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የመጥፋት እድላቸው  ሰፊ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢንስቲትዩት ሊጠፉ የደረሱ እንደ ቀበርቾ ፣ዳማካሴ፣ ኮሰረት፣ ሬት፣ ጌሾ፣ ጤና አዳምን የመሳሰሉ ሃገር በቀል ተፈላጊ እጽዋቶችን በመለየት ዝርያዎችን የማስመዝገብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አውሰተዋል።

ዘርፉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከግለሰብ እስከ መንግስት ትኩረት ማነስ፣ ኢኮኖሚያዊ  ሚናውን ያለመለየት ችግር እንዳለ አንስተው  ዝርያውን ከማስመዝገብ በተጨማሪ የእውቀት ክፍተቱን በስልጠና ለመሙላት እየተሰራ መሆኑን ተመራማሪው አስታውቀዋል።

ለአካባቢው አርሶ አደሮች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በዘርፉ ለተሰማሩ ተቋማትና ባለሃብቶች መነሻ ዘር ከመስጠት ባለፈ አካባቢውን መሰረት ያደረገ ችግኝ የማፍላት ስራ  ትኩረት መሰጠቱን አብራርተዋል።

እጽዋቶቹ በትንሽ ቦታ ብዙ ገንዘብ የሚያስገኙ ለበርካታ ዜጎች ስራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ በመሆናቸው መንግስት በግብርና ኤክስቴንሽን ውስጥ እንዲካተት ቢያደረገው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝ አስረድተዋል።

እጽዋቶቹ በእርጥብም ሆነ በማድረቅ ኤክስፖርት ማድረግ የሚቻል ምርቶች ከመሆኑም ባሻገር ለምግብና ለመድኃኒት ኢንዱስትሪው በብዓትነት ተፈላጊ መሆናቸውን  ተናግረዋል።

በዘርፉ በርካታ ክፍተቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ተመራማሪው በግብርና ኤክስቴንሽን ውስጥ በማካተት ምርታማነቱን ማሳደግና የግብይት ስርዓቱን በማሳለጥ ለባለሃብቶች ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

በማእከሉ የምግብ ሳይንስና ስነ ምግብ ኬምስትሪ ተመራማሪ  በሪሶ ሚኤሶ በበኩላቸው ማእከሉ በዘርፉ ብቸኛ የልህቀት ማእከል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከእጽዋቶቹ የሚገኘውን የይዘት ትንተና መስጠት የሚያስችል ላብራቶሪና የዘርፉ ባለሙያዎች የተሟሉለት መሆኑን ተናግረዋል።

መዓዛማና መድሃኒታማ እጽዋቶች ለምግብ፣ ለመድሃኒትና ለኮስሞቲክስ ፋብካሪካዎች ግብዓት የሚሆኑ ዘይቶች የሚመረትባቸው እንደሆኑም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የቅመማ ቅመም ሃመልማልና መዓዛማ እጽዋቶች አምራቾችና አቅራቢዎች ማህበር መስራችና የቦርድ ጸሃፊ አቶ አዲሱ ዓለማየሁ በስልክ በሰጡት አስተያየት ከዘርፉ በየዓመቱ እስከ 13 ሚሊየን ዶላር ገቢ ይገኛል።

በማህበሩ ውስጥ ከ110 በላይ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ከባለሃብቶቹ መካከል አራቱ የእስራኤልና የአሜሪካ ኩባንያዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ሮዝመሪ፣ጦስኝ፣በሶብላ፣ ሜንት ጨምሮ 24 የሚደርሱ መዓዛማና መድሃኒታማ እጽዋቶችን ወደ አውሮፓ ሃገራት እንደሚልኩ  ጠቁመዋል።

በመንግስት በኩል ለዘርፉ ትኩረት አልተሰጠውም የሚሉት አቶ አዲሱ በግብርና ኤክስቴንሽን ውስጥ አካቶ መስራት ቢቻል ከፍተኛ የስራ እድል የሚፈጥርና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ያሰፋል ብለዋል።

የወንዶገነት ግብርና ምርምር ማእከል በአትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንቲትዩት ስር ከሚገኙ 22 ምርምር ማእከላት አንዱና በመድሃኒታማና መዓዛማ እጽዋት ላይ የሚሰራ ብቸኛ ማእከል ነው።