ቢሮው በክረምት የዜግነት አገልግሎት ከ 7 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው

109

ጎባ ሰኔ 15.2014 (ኢዜአ) በዘንድሮው የክረምት የዜግነት አገልግሎት ከ 7 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን ለማከናወን እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የክረምት የዜግነት አገልግሎት መክፈቻን በመጽሐፍት ስጦታና በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር  በባሌ ሮቤ ከተማ ዛሬ አስጀምሯል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሰዓዳ ኡስማን እንዳሉት ቢሮው በክረምቱ የዜግነት አገልግሎት 7 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን ለማከናወን አቅዷል።

በክረምቱ ወቅት በዜግነት አገልግሎቱ ለመስራት ከታቀዱት ዋና ዋና ሥራዎች መካከል የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ፣ ደም ልገሳ፣ መጽሃፍት ማሰባሰብ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ ይገኙበታል።

በክረምቱ ወቅት በሚሰራው የዜግነት አገልግሎት ከመንግስት ካዝና ሊወጣ የሚችለውን 48 ሚሊዮን ብር ለማስቀረት መታቀዱን ነው የተናገሩት።

ቢሮው ዛሬ ለባሌ፣ ምስራቅ ባሌ፣አርሲ፣ ምዕራብ አርሲ ዞንና ሮቤ ከተማ ያደረገው የ5ሺህ መጽሃፍት ድጋፍ የክረምት የዜግነት አገልግሎቱ አካል መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ሰዓዳ የተደረገው ድጋፍ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እንደሚገመት አስረድተዋል።

በመክፈቻ ስነስርአቱ ላይ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በሮቤ ከተማ ጀኔራል ዋቆ ጉቱ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግቢ ችግኝ መትከላቸውም ተጠቅሷል።

ቢሮው ላደረገው የመጽሃፍት ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት የሮቤ ከተማው ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞቱማ  አስተዳደሩ በክረምት የዜግነት አገልግሎቱ ለምግብነት የሚውሉ በርካታ ችግኞች የመትከል ስራ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

ከመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ሮብዳ ጃርሶ በሰጡት አስተያየት በዜግነት አገልግሎት የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው።

የኦሮሚያ ባህልና ቱርዝም ቢሮ የ2014 ዓ/ም ዓመታዊ የዕቅድ ክንውንና የ2015 ዓ/ም ዕቅድ ላይ በባሌ ሮቤ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ግምገማ ተጠናቋል።

በግምገማው ላይ ከክልሉ የተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤቶች የተውጣጡ ባለሙያዎችና አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም