የኢትዮጵያና ህንድ ዲፕሎማሲ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል

140

ሰኔ 15/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያና ህንድ ዲፕሎማሲ በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ሱብራህማኒያ ጃይሻንካር ገለጹ።

የኢትዮጵያና የህንድ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አገራቱ በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ መስክ ተጠቃሚ በማድረግ ላለፉት 74 ዓመታት ዘልቋል።

በዛሬው እለትም የህንድ ኤምባሲ በአዲስ አበባ በአዲስ መልክ ያስገነባውን የኤምባሲ ህንጻ አስመርቋል።

በመረሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ሱብራህማኒያ ጃይሻንካር፤ ህንድና ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ አገራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱ ሀገራት በተለይም በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በትምህርት፣ በጤና እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የህንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በስፋት በመሰማራት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው የሁለቱ አገሮች ሁለንተናዊ ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር በቁርጠኝነት የምተሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ለረጀም ዘመናት የዘለቀው ኢትዮጵያና ህንድ ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ እንዲቀጥል የኢትዮጵያም ፍላጎት መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገልጸዋል።

ሁለቱ አገሮች በኢኮኖሚ ልማት፣ በንግድ ትስስር፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና ሌሎችም መስኮች ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው መሆኑንም አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ 637 የህንድ ኢንቨስተሮች በተለያዩ የልማት መስኮች ተሰማርተው እንደሚገኙም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ህንድ በአዲስ አበባ የሚገኘውን ኤምባሲዋን በአዲስ መልክ በመገንባት ማስፋፋቷ የትብብር ግንኙነቱን ለማጠናከር ያላትን ፅኑ አቋም ያመላከተ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያና የህንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እ.አ.አ በ1948 መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም