ማዕከሉ አምስት አዳዲስ የተሻሻሉ የሰብልና የጥራጥሬ ዝርያዎችን በምርምር አገኘ

337

ጎባ ሰኔ 15/2014/ኢዜአ/— የሲናና ግብርና ምርምር ማእከል አምስት አዳዲስ የተሻሻሉ የሰብልና የጥራጥሬ ዝርያዎችን በምርምር ማግኘቱን አስታወቀ።

በምርምር ማእከሉ የጥራጥሬና ቅባት ሰብሎች ከፍተኛ ተመራማሪና የሰብል ምርምር የስራ ሂደት ባለቤት  አቶ ታደለ ታደሰ ለኢዜአ እንደተናገሩት በምርምር የተገኙት የማካሮኒ እና ፓስታ ስንዴ፣ ባቄላ፣ ምስርና ሁለት የተልባ ዝርያዎች ናቸው።

በምርምር የተገኙት ዝርያዎች በሽታን በመቋቋም ከነባር ዝሪያዎች  ከ14 እስከ 19 በመቶ ብልጫ ያለው ምርት የመስጠት አቅም ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሽታንና ተባዮችን  የመቋቋም አቅም ያላቸው እንደሆኑ አመልክተዋል ።

ዝርያዎቹ ባለፈው ወር ብሄራዊ ዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ መጽደቃቸውን አስታውቀዋል።

በተለይም በምርምር የተገኘው አዲስ የማካሮኒና ፓስታ ስንዴ በሄክታር 62 ኩንታል ምርት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል ።

ዝርያው በቅርብ ዓመት በምርምር ማዕከሉ ተለቆ በመመረት ላይ ከሚገኛው “ቡላላ” ከተሰኘ የስንዴ ዝርያ በ12 ነጥብ 5 በመቶ የምርት ብልጫ ያለው መሆኑን ተናግረዋል ።

አዲስ የተለቀቀው የባቄላ ዝርያም በሄክታር በአማካኝ 35 ኩንታል ምርት የሚሰጥና ባለፈው ዓመት በማዕከሉ ከተለቀቀው “ቶሻ” ከተሰኘ የባቄላ ዝርያ በ14 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ ያለው ምርት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

የባቄላ ዝርያው ለባሌ ከፍታማ ቦታዎችና ተመሳሳይ ስነምህዳር ላላቸው የአገሪቱ ቦታዎች አዲስ ዝሪያ ሆኖ በኮሚቴው እንዲጸድቅ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

አዲስ የተለቀቀው የምስር ዝርያም  በሄክታር በአማካኝ ከ24 እስከ 27 ኩንታል ምርት የሚሰጥና ከነባሩ ዝርያ በ11 ነጥብ 4 በመቶ  የምርት ብልጫ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የተልባ ምርቶቹም በሽታዎችና ተባዮችን የሚቋቋሙ ከመሆናቸው በተጓዳኝ ከፍተኛ የዘይት ይዘት ስላላቸው አርሶ አደሩ በስፋት የሚያመርታቸው ከሆነ በአገር ውስጥ የተከሰተውን የዘይት እጥረትን በመቅረፍ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ታምኖባቸዋል” ብለዋል፡፡

የብሔራዊ ዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ ለባሌ ደጋማና ወይና ደጋ  ስነምህዳር እና በአገሪቱ ተመሳሳይ ስነምህዳር ላላቸው ቦታዎች መመረት እንዲችል አዲስ ዝርያ ሆነው እንዲጸድቁ መወሰኑን አቶ ታደለ ጨምሮ ገልጸዋል፡፡

የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታመነ ሚደቅሳ በበኩላቸው ማዕከሉ የአርሶና አርብቶ አደሩን ችግርና ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አዳዲስ ዝርያዎችን በምርምር የማፍለቅና የማላመድ ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምርምር ማዕከሉ ባለፉት ዓመታት ባደረገው የስራ እንቅስቃሴ አዳዲሶቹን ዝርያዎች ሳይጨምር 10 የማካሮኒ እና የፓስታ ስንዴ፣ 5 የባቄላ፣ 3 የምስርና 3 የተልባ ዝርያዎችን ለተጠቃሚው ማድረሱን አመልክተዋል፡፡

አቶ ታመነ እንዳሉት እነዚህ  የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች አርሶ አደሩ ጋር እንዲደርሱ የዘር አባዥ አካላት በበቂ መጠን ዘሩን አባዝተው ተፈላጊውን ውጤት ማግኘት ይቻል  ዘንድ የበከላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

ከሲናና  ወረዳ ሞዴል አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር  አብዳ ከማል በሰጡት አስተያየት በእጃቸው የሚገኘው የቦሎቄ ዝርያ ዝቅተኛ ምርት ከመስጠቱም በላይ በበሽታ ስለሚጠቃ የልፋታቸውን ያክል ምርት አግኝተው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉት አሁን የምርምር ማእከሉ ያወጣውቸውን ዝርያዎች  የመነሻ ዘር በመቀበል ለማባዛት ፍላጎት እንዳለቸው ጠቁመዋል፡፡

ማዕከሉ በአካባቢያቸው ከአርሶ አደሩ ጋር በማሳ ላይ በሚያደርገው ምርምር በምርጥ ዘርና ሌሎችም የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮች አጠቃቀም ላይ እውቀት ማግኘታቸውንና በዚህም ምርታማነታቸው እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የወረዳው አርሶ አደር አቶ አብዱልከሪም ሀጂ ናቸው፡፡

በ1978 ዓ.ም የተቋቋመው የሲናና ግብርና ምርምር ማእከል  እስከ አሁን 93 በምግብ እህልና በእንስሳት መኖ ላይ ያተኮሩ የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚው ማድረሱን ከምርምር ማእከሉ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡