ኢንስቲትዩቱ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ እንዳይከሰት የቁጥጥርና ቅኝት ስራዎች እንዲጠናከሩ አሳሰበ

78

ሰኔ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዓለም ስጋት እየሆነ የመጣው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ እንዳይከሰት የቁጥጥርና ቅኝት ስራዎችን ከወትሮው በተጠናከረ መልኩ ማከናወን እንደሚገባ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ በአፍሪካ እስካሁን በስምንት አገራት መከሰቱንም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፤ ለህብረተሰቡ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልእክት ያለውን መግለጫ ለኢዜአ ልኳል።

በመግለጫውም የዓለም ስጋት ሆኖ ከቀጠለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተጨማሪ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝም ከዚህ በፊት ባልተከሰተባቸው 30 አገራት ተከስቶ ከ1 ሺህ 217 በላይ የበሽታው ታማሚዎች ሪፖርት መደረጉን ተጠቁሟል።

በአፍሪካም በስምንት አገራት መከሰቱ ተረጋግጦ 1 ሺህ 536 የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች መገኘታቸው ታውቋል።

በኢትዮጵያ የወባ፣ ኩፍኝ እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እየተባባሰ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው የቁጥጥር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብሏል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ እንዳይከሰትም የቁጥጥርና ቅኝት ስራዎችን ከወትሮው በተጠናከረ ሁኔታ ማከናወን ይገባል ብሏል።

የቁጥጥርና ቅኝት ስራው እንዳለ ሆኖ ተጠርጣሪዎች ካጋጠሙ ህብረተሰቡ ለጤና ተቋማት ሪፖርት እንዲያደርግም ተጠይቋል።

ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ የኮሌራና ሌሎች ውሀ ወለድ በሽታዎች የመከሰት አጋጣሚዎች ስለሚኖሩ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በተለያዩ ቦታዎች ውሀ ያቆሩ ጉድጓዶችን በማጥፈፍ የወባ ትንኝ መራባትን መከላከልና በኬሚካል የተነከረ አጎበር ስርጭትን ማጠናከር ይገባል ብሏል።

ለህብረተሰቡ የጤና ስጋት የሆኑ ወረርሽኖችን ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት አስፈላጊውን  የዝግጅትና የመከላከል ስራ እንዲያከናውኑም ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም