አሰቃቂ ግድያ የፈጸሙ አራት ግለሰቦች እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ እስራት ተቀጡ

183

ሚዛን፣ ሰኔ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቤንች ሸኮ ዞን ደቡብ ቤንች ወረዳ ስድስት ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ የፈጸሙ አራት ግለሰቦች እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ማሳለፉን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።  

የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ቢንያም ባቡ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት ቅጣቱ የተላለፈው በነፍስ ማጥፋት ወንጀል በተከሰሱት 1ኛ ተከሳሽ ካባ ሙሉጌታ፣ 2ኛ ተከሳሽ ማንታል ጉሉ፣ 3ኛ ተከሳሽ ማስረሻ አለማየሁ እና 4ኛ ተከሳሽ ኤልያስ ታጳ በተባሉ ግለሰቦች ላይ ነው።

እነዚሁ የደቡብ ቤንች ወረዳ ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦች ሚያዝያ 19 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 6 ሰዓት እስከ ምሽቱ 9 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ የተለያዩ የጦር እና የስለት መሳሪያዎችን በመያዝ በስድስት ሰዎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ እንዲሁም የዘረፋ ወንጀል መፈጸማቸውን የክስ መዝገባቸው እንደሚያትት ገልጸዋል።

ግለሰቦቹ ወንጀሉን ፈጽመው ለመሰወር ቢሞክሩም በህዝብ ጥቆማና በፖሊስ ክትትል ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ተይዘው በከባድ የሰው ግድያ እና ውንብድና ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ጠቁመዋል።

ተከሳሾች ከገደሏቸው ስድስት ሰዎች መካከል ሦስቱን ባሉበት ቤት ውስጥ እሳት በመለኮስ ያቃጠሉ  መሆናቸውን የክስ መዝገባቸው  እንደሚያትትም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

ተከሳሾች ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው በሰውና ሰነድ ማስረጃ ተረጋግጦባቸው መከላከል ባለመቻላቸው  ፍርድ ቤቱ የጥፋተኛነት ብይን መስጠቱን ተናግረዋል።

ይህንን ተከትሎ ጉዳያቸውን ሲከታተል የቆየው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራቱን ተከሳሾች ከ25 ዓመት እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ ፅኑ አስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ተላልፏል።

በዚሁ መሠረት ፍርድ ቤቱ ዛሬ ባስቻለው ችሎት 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ሲወስን፤ 1ኛ እና 4ኛ  ተከሳሾች ደግሞ ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የወንጀል ሪከርድ ስላልተገኘባቸው እያንዳንዳቸው በ25 ዓመት ጽኑ አስራት እንዲቀጡ ውሳኔ መተላለፉን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።