የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት በብዙ መልኩ ውጤት እየታየበት ነው- የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል

117

ሰኔ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) “የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ መርሃ ግብር አካል የሆነው “አዲስ ለልጆቿ” በተማሪዎች የደምብ ልብስ (ዩኒፎርም) የትውውቅ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት በብዙ መልኩ ውጤት እየታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

የአገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አቅርቦትን በመጀመር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የውጭ ምንዛሪን በማዳን ተጨባጭ ውጤት ተገኝቶበታል ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በከተማዋ  ተግባራዊ የተደረገው የተማሪዎች የደንብ ልብስ ጫማና ቦርሳ በሀገር ውስጥ እንዲመረት መደረጉ ከፍተኛ ወጭ ማዳኑን ጠቅሰው በቀጣይም በልዩ ትኩረት ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የተጀመረው ይህ በጎ ጅምር በሌሎች አካባቢዎችም በጥሩ ተሞክሮነት ተወስዶ የማስፋት ስራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ፤ ከሁለት ዓመት በፊት የጀመረው የተማሪዎች የደንብ ልብስና ምገባ ፕሮግራም የሚደነቅ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚሁ መርሃ -ግብር የምንጠቀምባቸው ቁሳቁሶች በሀገር ውስጥ መመረታቸው ደግሞ የላቀ አገራዊ ጥቅም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የምገባ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አንቺነሽ ተስፋዬ በበኩላቸው በዚሁ ፕሮግራም ከ799 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት እንዲያገኙ ከ13 ሺህ በላይ እናቶች በዚሁ ፕሮግራም የስራ እድል የተፈጠረላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በ”አዲስ ለልጆቿ”  የደምብ  ልብስ የትውውቅ መርሐ-ግብር በተማሪዎች የፋሽን ትርዒት የቀረበ ሲሆን ለፕሮግራሙ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለድርሻ አካላትና ተቋማትም ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡