የአፍሪካ -ኢሲያ የፓርላማ ጉባዔ በአዲስ አባባ በመካሄድ ላይ ነው


ሰኔ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአፍሪካ - ኢሲያ ሀገራት የፓርላማ አባላት የትብብር ጉባዔ በ አዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ጉባኤው ከአፍሪካ እና ኢሲያ ሀገራት ለተወጣጡ የፓርላማ አባላት በሥነ- ሕዝብ እና የልማት ጉዳዮች እንዲሁም ምክር ቤታዊ ተግባራትን በመወጣት ዙሪያ እየመከረ ነው፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ደሳለኝ ወዳጆ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ለጉባዔው መሳካት ድጋፍ ያደረጉ የኢሲያ ሀገራትን አመስግነዋል፡፡

በጉባኤው የ2030 የዕድገት እና የልማት ዕቅድ በተለይም የትምህርት፣ የመሠረተ-ልማት እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ ውይይት ይካሄዳል ተብሏል፡፡

እንዲህ ዓይነት ጉባዔዎች የምክር ቤቶች የጋራ መማማሪያ መድረክ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሥነ-ሕዝብ (UNFPA) ዳይሬክተር አማካሪ ማቢንጉዌ ንጎም በበኩላቸው ጉባዔው ምክር ቤቶች ለሚያደርጉት የሰላም፣ የደኅንነት እና የዕድገት ተግባራት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ለዚህ የጋራ ምክክር ድጋፍ ያደረጉትን በኢሲያ የጃፓን ትረስት ፈንድ እና የኢሲያ ሥነ-ሕዝብ እና ልማት ማኅበርን አመስግነዋል፡፡

ማቢንጉዌ አክለውም፤ መድረኩ ምክር ቤቶች ሕጎችን በማውጣት ሕዝባዊ ኃላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ እንዲወጡ የሚያስችል የልምድ መለዋወጫ እንደሆነም ጠቁመዋል ሲል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም