የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ዓለምን እየፈተነ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ አይነተኛ መፍትሄ ነው --በኢትዮጵያ የሩሲያና ህንድ አምባሳደሮች

118

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ዓለምን እየፈተነ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ አይነተኛ መፍትሄ መሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያና ህንድ አምባሳደሮች ገለጹ።

ሩስያና ሕንድ በአረንጓዴ ልማት መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡

አራተኛው ዙር አገር-አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የተሳተፉት በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ያቭጊኒ ተርኪን በዓለም ላይ ሚሊዮኖችን እየተፈታተነ ያለውን የአየር ንብርት ለውጥ ለመቋቋም የተባበረ አቅም እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከአራት ዓመታት በፊት የጀመረችው አረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የህዝብን ኑሮ ለመለወጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልፀው፤ ከዚህ አኳያ መርሃ-ግብሩ ለሌሎች አገራትም ምሳሌ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ዓለም ለምትፈተንበት አየር ንብረት ለውጥ አይነተኛ መፍትሄ እንደሆነ ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም ለቀጣይ ትውልድ መሰረት የሚሆን ትልቅ ፕሮጀክት እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም እርሳቸውን ጨምሮ በአዲስ አበባ የሚገኙ የሌሎች አገራት ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ንቅናቄውን ደግፍው በመርሃ-ግብሩ ላይ መገኘታቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱ አገራት ከኢትዮጵያ ጋር በአረንጓዴ ዲፕሎማሲው መስክ በጋራ እንደሚሰሩም አምባሳደሮቹ አረጋገጠዋል።

ሰፊ ግዛት ያላት ሩስያ ለዓለም ኦክስጅን የሚሰጡ የተፈጥሮ ደኖች እንዳሏት ገልጸው፤ ያም ሆኖ አሁንም ደኖችን መንክባከብ ላይ ጥረት እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ በሚገኘው የሩስያ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ የደን ልማት እየተከናወነ መሆኑን  አረጋግጠዋል።

አምባሳደር ሮበርት በበኩላችው ህንድና ኢትዮጵያ አረንዴ ልማትን ጨምሮ በሁሉም መስኮች ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የሕንድ ኤምባሲ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እየተሳተፈ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም