ችግኝ መትከል ለአፋር አርብቶ አደር የህልውና ጉዳይ ነው-አቶ አሊ ሁሴን

132

ሰመራ፣ ሰኔ 14/2014(ኢዜአ) ችግኝ መትከል ለአፋር አርብቶ አደር የህልውና ጉዳይ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማእረግ የክልሉ ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አሊ ሁሴን አስታወቁ።


በክልሉ የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ዛሬ በሰመራ ከተማ ተካሂዷል።


በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማእረግ የክልሉ ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አሊ ሁሴን በወቅቱ እንደተናገሩት እንደ ሀገር የተጀመረው የአረንጎዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር የእንስሳት ሃብቱ የኑሮ መሠረቱ ለሆነው አርብቶ አደር ትርጉሙ ብዙ ነው።


የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩ የተፈጥሮ ሚዛንን ከመጠበቅ በተጨማሪ ለሰውና እንስሳት ምግብነትና መድሃኒትነት ሊውሉ የሚችሉ ዛፎች ጨምሮ እጽዋቶችን በማልማት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።


“መርሃ-ግብሩ በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ ምከንያት በክልሉ እየጨመረ የመጣውን በረሃማነት ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ ነው” ብለዋል።


ባጠቃላይ በመርሀ ግብሩ የሚተከሉ ችግኞች ለአርብቶ አደሩ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን አስታውቀዋል ።


የክልሉ አርብቶ አደር ይህንኑ በመገንዘብ በችግኝ ተከላው ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል ።


በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችም የችግኝ ተከላውን እንዲሁም የእንክብካቤና የማጽደቅ ስራውን በባለቤትነት በመምራት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።


የአፋር ክልል እንስሳት፣እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ኡስባን በበኩላቸው የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የችግኝ ተከላ በዛሬው እለት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች መጀመሩን አስታውቀዋል።


በመርሃ-ግብሩ 14ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል መታቀዱን ጠቁመው በዛሬው ቀን ብቻ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ አመልክተዋል ።


መርሃ ግብሩን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ በየደረጃው ባሉ አመራሮች የሚመራ አደረጃጀት መፈጠሩን ጠቁመው እያንዳንዱ የሚተከል ችግኝ በአቅጣጫ መጠቆሚያ (ጂ ፒ ኤስ) ውስጥ ገብቶ የመጽደቅ ምጣኔንና ተያያዥ ጉዳዮች ክትትል እንደሚደረግ አስታውቀዋል።


በኢትዮጵያ ዛሬ ስድስት ቢሊዮን ችግኞች የሚተከሉበት አራተኛው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ይፋ መሆኑ ይታወቃል።


ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ