የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ለጀግና ቤተሰቦች የገበያ ቦታ አስረከበ

136

ባህር ዳር፤ ሰኔ 14/2014 (ኢዜአ)፡ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በህግ ማስከበር ዘመቻው ግንባር ዘምተው ህይወታቸውን ላጡ 14 የጀግና ቤተሰቦች የገበያ ቦታ አስረከበ።

የከተማ አስተዳደሩ አገልግሎቶች አቅርቦት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዘላለም ታፈረ እንደገለጹት የገበያ ቦታው በዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ''ጋጃ መስክ'' ተብሎ በሚጠራ የገበያ ማዕከል የሚገኝ  ነው።

 ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ከአሸባሪው ህወሓት ለመታደግ ሲፋለሙ ለተሰው የፖሊስ፣ የሚሊሻ እና ፋኖ ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው 4 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ መሰጠቱን ተናግረዋል።

የገበያ ቦታው ለሀገርና ህዝብ  ሲሉ መስዋትነት የከፈሉ ጀግኖች ቤተሰቦች   እንዳይቸገሩ መተዳደሪያ እንዲሆናቸው ታስቦ መሰጠቱን ተናግረዋል።

የገበያ ቦታውን ከተረከቡት መካከል የጀግና ሚሊሻ ባለቤት የሆኑት ወይዘሮ ካሣነሽ ክንዴ መንግስት ለሰጣቸው የገበያ ቦታ አመስግነዋል።

ቀደም ሲል በባለቤታቸው ገቢ ይተዳደሩ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ግን ምንም አይነት ገቢ የሌላቸው በመሆኑ ወደ ስራ ለመግባት ባለሀብቶችና  መንግስት የመቋቋሚያ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

''የከተማ አስተዳደሩ የገበያ መስሪያ ቦታ መስጠቱ በዘላቂነት ለመቋቋምና የሌሎችን እርዳታ ከመጠበቅ ለመላቀቅ ያስችላል'' ያለችው ደግሞ የጀግና ሚሊሻ ልጅ ወጣት ህሊና ይማራል ናት።

አባቷ ለሀገርና ለህዝብ ድህንነት ሲል በጀግንነት መስዋቱ ሁሌም ሲያኮራት እንደሚኖር ጠቅሳ፤ መንግስት የጀግኖችን ውለታ ባለመርሳት ቤተሰቦቻቸውን ለማገዝ  እየሰራ ያለው ስራ  የሚያስመሰግነው መሆኑን ተናግራለች።

የተሰጠው የገበያ መስሪያ ቦታ በአግባቡ አገልግሎት ላይ በመዋል ተጠቃሚ እንድትሆን ባለሀብቶችና ህብረተሰቡ በመተባበር የማቋቋሚያ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቃለች።

በከተማ አስተዳደሩ በህልውና ዘመቻው ተሳትፈው መስዋትነት ለከፈሉ የጀግና ቤተሰቦች የገበያ ቦታና የመኖሪያ ቤት ድጋፍ እንደሚደረግ ቀደም ሲል የከተማ አስተዳደሩ መወሰኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም