ለብሔራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተጠቆመ

130

ሶዶ፤ ሰኔ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለሀገር ሰላም ግንባታና አንድነት ቁልፍ ሚና ይጫወታል ተብሎ ለታመነበት ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።

ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ምሁራኑ ጠቁመዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዲላና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨሲቲዎች ምሁራን እንደገለጹት ብሔራዊ ምክክሩ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ነው።

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አበሻ ሽርኮ እንዳሉት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ሀገራዊ ምክክር አድርገው ከተሳካላቸውና ከከሸፈባቸው ሀገራት ተሞክር መውሰድ ይገባል።

ምክክሩ አካታችና የሁሉንም ስብጥር ያካተተ መሆኑን እንዳለበት አመልክተው፤ ከሌሎች ሀገራት ልምድ በመውሰድና ችግሮችን በመፍታት ጠንካራ ሀገር መገንባት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በፖለቲካ ተፅዕኖ ውስጥ የገቡና የመንግስት ጣልቃ ገብነት የነበረባቸው ሀገራት ያካሄዱት ሀገራዊ ምክክር ስኬታማ አለመሆኑን አመልክተዋል።

”አካታች ብሔራዊ ምክክሩ የተወሰኑ ቡድኖችን ብቻ መሰረት ያደረገ ሊሆን አይገባውም” የሚሉት ዶክተር አበሻ፤ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያልነበረባቸውና ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነጻ የሆኑ ሀገራት ባካሄዱት ሀገራዊ ምክክር ስኬታማ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ኬንያና ሩዋንዳን ለአብነት የጠቅሰው ምሁሩ፤ ጠንካራና ሰላሟ የተረጋገጠ ሀገር ለመገንባት የነገን ተስፋና መጻኢ እድል ማሰብ እንደሚገባው አመልክተዋል።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አብዱ መሐመድ በበኩላቸው ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

”ዛሬን መመካከር ነገን በተሻለ መልኩ ለመገንባት ያስችላል” ያሉት ምሁሩ፤ ሁሉም ዜጋ በኃላፊነት ስሜት ለምክክሩ ስኬት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

የምክክር መድረኩ ሊሳካ የሚችለው በአንድ ወገን ጥረት ብቻ አለመሆኑን የገለጹት ዶክተር አብዱ፤ ”ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የነቃ ተሳትፎ ማድረግ መብቱ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ግዴታው መሆኑን በመገንዘብ ሊሳተፍ ይገባል” ብለዋል።

መድረኩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ያገባኛል በሚል መንፈስ ሀሳቡን የሚያዋጣበት እንዲሆን መደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የሀገሪቱን ችግሮች በውይይት እንጅ በሃይል መፍታት እንደማይቻል ጠቁመው፤ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት የሀሳብ ልዕልና ስልጣኔ መሆኑን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል ብለዋል።

ህዝብ አድማጭ ብቻ ሳይሆን ተደማጭም መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

በሀገሪቱ ላይ የተጋረጡ  ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በመፍታት ሰላምን በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገበ ምሁራኑ አመላክተዋል።