ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ተፅዕኖ ፈጣሪነቷና አጋርነቷ ጎልቶ እንዲወጣ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲው ቀጣናዊ ትስስር እንዲኖረው ተደርጓል

85

ሰኔ 14/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ተፅዕኖ ፈጣሪነቷና ሁነኛ አጋርነቷ ጎልቶ እንዲወጣ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲው ቀጣናዊ ትስስር እንዲኖረው መደረጉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

አራተኛው ዙር የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በይፋ አስጀምረዋል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት 18 ቢሊየን ችግኝ በመትከል ስኬታማ እንቅስቃሴ አድርጋለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ለቀጣናው አገራት ጨምሮ ለመላ አፍሪካውያንና ለዓለም ምሳሌ የሚሆን የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ማከናወኗን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላት ቀጣናዊ ትስስርና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ በሰላም፣ በልማት፣ በችግር ፈችነቷና በሁነኛ አጋርነት መታየት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በኢኮኖሚያዊና በመሰረተ-ልማት ዘርፎች ያላትን ትብብር በአረንጓዴ አሻራ ዲፕሎማሲም በላቀ ሁኔታ ለማስቀጠል እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በአፍሪካ ቀንድ ተፅዕኖ ፈጣሪነቷና ሁነኛ አጋርነቷ ጎልቶ እንዲወጣ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲው ቀጣናዊ ትስስር እንዲኖረው ተደርጎ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ የገጠሟትን አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች አሸንፋ ትንሳኤዋን እውን ታደርጋለችም ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተመዘገቡ ስኬቶች በሰላምና ጸጥታ፣ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች መድገም ይገባልም ብለዋል፡፡

በመሆኑም መንግሥት ከችግኝ ተከላ ጎን ለጎን የዜጎችን ህይወት እየቀጠፉ በሚገኙ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ አስደናቂ ውጤት እያሰመዘገበች መሆኗን ተናግረዋል።

በመርሃ-ግብሩ እየተመዘገቡ ያሉ ሥራዎች መልካም ቢሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ ቀጣይነት ባለው መንገድ ሊሰራበት ይገባልም ብለዋል፡፡

የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ሁሉም ሊሳተፍበት የሚገባ የጋራ ኃላፊነት መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም