በጎንደር ከተማ በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባው የዳቦ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ እየተፋጠነ ነው

72

ጎንደር፣ ሰኔ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የዳቦ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላትና የከተማው አመራሮች የፋብሪካውን የግንባታ ሂደት ተመልክተዋል።

የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ተስፋነህ እንደተናገሩት፤ ፋብሪካው በቀን 400 ሺህ ዳቦ በማምረት ለተጠቃሚዎች የማቅረብ አቅም አለው።

የፋብሪካው ግንባታ የዳቦና የዱቄት ማምረቻን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለፉት አራት ወራት በተደረገ ጥረት ግንባታው በመልካም ሁኔታ መሄዱን ተናግረዋል፡፡

የግንባታ ፕሮጀክቱ በመጪዎቹ አምስት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የፋብሪካው ግንባታ በ10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ማረፉን የጠቆሙት የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ በተያዘለት ጊዜ አጠናቆ ለማስረበከብ ጥረት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

ፋብሪካው በግንባታ ወቅት ለ42 ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰው፤ በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት ሲገባ ለበርካታ ወጣቶች ተጨማሪ የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው የፋብሪካው መገንባት ለጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በቂ የዳቦ ምርት ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ለፋብሪካው ግንባታ መሳካት የግንባታ ቦታ በነጻ ከመስጠት ጀምሮ ግንባታው ያለበትን ሁኔታ በየጊዜው በመከታተል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የፋብሪካውን የስንዴ አቅርቦት ለመሸፈን ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም