የተፈጥሮ እስትንፋስ – አረንጓዴ አሻራ

652

የኢትዮጵያ የደን ሃብት ከግብርና፣ ከማገዶ፣ ከከሰል ማክሰል፣ ከልቅ ግጦሽ፣ ከግንባታና ከእንጨት ስራ ጋር በተያያዘ  በማይታመን ፍጥነት መጠኑ ሲቀነስ እያስተዋልን ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡

ኢትዮጵያ በደን ሃብቷ ከአፍሪካ ሀገራት ግንባር ቀደም የነበረችባቸው ዘመናት የማይረሱ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የህዝብ ብዛት፣ የእርሻና የግጦሽ መሬት እጥረት እንዲፈጠር በማድረጉ ሰዎች የደን ሃብቱን ያለመሰሰት በመጨፍጨፍ መሰረታዊ ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉ አስገድዷቸዋል፡፡

ሀገሪቷን በተለያዩ ዘመናት ያስተዳደሯት መንግስታት የደን ሃብቱን ለመንከባከብ የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርጉም  ሙከራቸው ያዝ ለቀቅ ስለነበር የታሰበውን ውጤት ማሳካት አልቻለም፡፡

የደን ሃብት ከሰብዓዊ ህይወት ጋር ያለውን ቁርኝት ሁሉም ባይዘነጉትም የሰጡት ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ ሀገሪቱ አሁን ላይ እየገጠማት ላለው የተፈጥሮ አደጋና ድርቅ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ተጠያቂ ናቸው፡፡

ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣበት እለት አንስቶ ችግሩን ለመቅረፍ በቁርጠኝነት እየተገበረው ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከፍተኛ ለውጥ እያስገኘ ነው፡፡

መርሃ ግብሩ ቀደም ብለው ከተጀመሩት ጥረቶች በተለየ በጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በመተግበሩ አሁን ላይ አለም አቀፍ ምስጋና የተቸረው ውጤት ማሳየት ችሏል፡፡

መርሃ ግብሩ አገሪቱን በድጋሚ አረንጓዴ ገጽታ በማላበስ፣ የገጠሩን ማህበረሰብ ህይወት በማሻሻል የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም መልክዐ ምድር በመገንባት በኩል የተሳካ የሚባል ውጤት አስገኝቷል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሐምሌ 2011 ዓ.ም ያስጀመሩት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአራት አመት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኝ መትከልን አላማ አድርጎ የተጀመረ ሲሆን በዚህም በመጀመሪያው አመት ብቻ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል እቅዱን ሙለ በሙሉ ማሳካቱ አይዘነጋም፡፡

በመቀጠል በ2011 ዓም 5 ቢሊዮን ችግኝ፣ በ2012 ዓም  6 ቢሊዮን እንዲሁም በ2013 ዓም 7 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የተደረገው ጥረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጥላ ቢያጠላበትም ከሞላ ጎደል ስኬታማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) 75 ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር “የእኛ ዋነኛ ግብ የተራቆተውን መሬት በደን መሸፈንና የተሻለ ነገን መፍጠር ብቻ ሳይሆን ስራችንን አረንጓዴና ከአየር ፀባይ ለውጥ ጋር በተስማማ መልኩ ማከናወን ነው፣ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንዳለብን የሚያሳስበን ተጨማሪ ነጋሪ አያስፈልገንም፣ ምክንያቱም  የአየር ፀባይ ለውጥ የሚያስከትለውን አውዳሚ ተጽእኖ በመላው አለም በተለያዩ ቦታዎች ላይ በተጨባጭ አይተነዋል “ በማለት ለመርሃ ግብሩ ስኬታማነት ያላቸውን ቁርጠኝነታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በ2011 ዓ.ም ሐምሌ ወር በተደረገው የመጀመሪያ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በአንድ ቀን ብቻ 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ግብ ቢያስቀምጥም አብላጫ በሆነ መጠን 354 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል በአለም አቀፍ ደረጃ የመነጋገሪያ ርዕስ ለመሆን ችሏል፡፡

በዚሁ ወቅት 23 ሚሊዮን ሰዎች በችግኝ ተከላው ላይ በመሳተፍ 4 ነጥብ 75 ቢሊዮን  ችግኝ በመትከል ከእቅድ በላይ አፈጻጸም አሳይተዋል፡

የአረንጓዴ አሻራው ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ፣አካባቢያዊና ፖለቲካዊ አበርክቶዎች

የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነስ በመምጣት አሁን ላይ ከአገሪቱ የቆዳ ስፋት 15 በመቶ ወይም 17 ሚሊዮን ሄክታር ብቻ መሸፈኑን በቅርቡ የወጣው “Mass tree planting Prospects for a green legacy in Ethiopia“ የተሰኘ ሪፖርት ያሳያል፡፡

ከዚህ ውስጥ 15 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታሩ የተፈጥሮ ደን ሲሆን የተቀረው በችግኝ ተከላ የተሸፈ መሆኑን ሪፖርቱ  ያሳየ ሲሆን በተጨማሪ ሀገሪቱ በደን ምንጠራ ባዶ የሆነና ደንን መልሶ ለማልማት ምቹ የሆነ 18 ሚሊዮን ሄክታር ባዶ መሬት እንዳላት ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በሀገሪቱ ዋነኛ የደን ጭፍጨፋ መንስዔ የሚባሉት የግብርና ልማት ማስፋፊያ፣ ከሰል ለማክሰልና ለግንባታ በሚል የሚቆረጠው እንጨት መጨመር፣ ልቅ ግጦሽና የሰፋፊ እርሻዎች መስፋፋት ሲሆኑ በተለይ በጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሰፋፊ እርሻ ልማት መብዛት በአካባቢው ለሚታየው የደን መመናመን ምክንያት መሆናቸውን ጥናቱ ያሳያል፡፡

ለዚህ ደግሞ የህግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ ደንብ አለማዘጋጀት፣ የማስፈጸም አቅምና ፖሊሲ ደካማነት በምክንያትነት ሲጠቀሱ አስተማማኝ ያልሆነ አካባቢያዊ የመሬት ኪራይ እንዲሁም የደን አጠቃቀም መብት አለመቀመጡ ችግሩን ማባባሳቸው ተመላክቷል፡፡

በመላው አለም የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያለፉትን ሁለት አመታት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በታሰበው ልክ እንዳይከናወን እንቅፋት ቢፈጥርም መንግስት የተከተለው የጥንቃቄ እርምጃ  ስኬቱን ለማስቀጠል አስችሏል፡፡

ያም ቢሆን ባለፈው አመት ለተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 22 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኝ መትከል ተችሏል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ሀገር በቀል እሳቤ ከመሆን ባለፈ ባለቤቱና ተጠቃሚው ህዝቡና ህዝቡ ብቻ  በመሆኑ በዚህም በመርሃ ግብሩ በመታገዝ በርካታ የስራ ዕድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን በተለይ ወጣቶችና ሴቶች ችግኝ በማፍላትና በመንከባከብ በስፋት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ መርሃ ግብሩ የተሻሻለ የግብርና አሰራር በማስፈን፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የውሃ ሃብትንና የብዝሃ ህይወት ጥበቃን በማረጋገጥ ዘላቂ ተጠቃሚነትን እንደሚያስገኝና፣ በተጨማሪም አለም አቀፍ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የራሱን አስተዋጽኦ በማበርከት የግሪን ሀውስ ጋዝን ለመቀነስ እንደሚረዳ ተረጋግጧል፡፡

ሀገር አቀፉ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከተሞችን ከማስዋብ ባለፈ በዙሪያቸው የሚገኙና የተበከሉ ወንዞችን ደህንነት በማስጠበቅ የአረንጓዴ ውበት ማስጠበቂያ ቦታዎችን በዋና ዋና ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል፡፡

ከሁሉም በላይ የተጀመረው መርሃ ግብር የጎረቤት ሀገራትን ትኩረት በመሳብ ለጋራ ተጠቃሚነት በጋራ እንዲሰሩ ከማነሳሳት ባለፈ በቀጠናው በግጦሽ መሬት፣ በውሃና በደን ሃብት እጥረት የሚፈጠረውን ግጭት በማስወገድ ስደትንና ከመኖሪያ ቀዬ መፈናቀልን ለማስቀረት ያስችላል፡፡

ኢትዮጵያ አንድ ቢሊዮን ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት መላኳን መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን በዚህም እ.አ.አ በ 2021 ጂቡቲና ደቡብ ሱዳን በመርሃ ግብሩ ለመታቀፍ ያላቸውን ዝግጁነት አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ሀገሪቱ ባደረገችው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ መራጮች ድምጽ ከሰጡ በኋላ ችግኝ እንዲተክሉ በመቀስቀስ ሁለንተናዊ ለውጡን እውን ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት ማሳየት ተችሏል፡፡

ለወጣቶች ያስገኘው አበርክቶ

በየአካባቢው የሚኖሩ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ከሀገራዊው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማግኘት የቻሉ ሲሆን በዕድሉ በመጠቀም  ችግኝ በማፍላትና በማቅረብ፣ ጉድጓድ በማዘጋጀትና ችግኞችን በመንከባከብ የራሳቸውን ገቢ አግኝተዋል፡፡

በግላቸው ችግኝ የሚያፈሉ ወጣቶች በተጀመረው መርሃ ግብር በመነቃቃት አመቱን ሙሉ የዛፍ ፣የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን ለግለሰቦችና ድርጅቶች በመሸጥ ገቢያቸውን ከፍ አድርገዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ተጠቃሚዎች ችግኞቹን በአደባባዮች፣ በፓርኮችና፣ በመኖሪያ ቤታቸውና በስራ ቦታቸው ላይ በመትከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩት ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ኃላፊነት እየተወጡ ነው፡፡

ይህ ተግባር በቀጣይ ግለሰቦች መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ችግኞችን በማፍላት ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ በማሳየት ተነሳሽነታቸውን ከማሳደጉ ባለፈ ለወጣቶች ተጨማሪ የስራ ዕድል ይፈጥራል፡፡

የችግኝ ተከላው ሲጀመር የነበረው ግንዛቤ አነስተኛ እንደነበር ያስታወሰው ሪፖርት በቀጣይ አመታት ጉድለቶችን በመሙላትና ለተጠቃሚዎቹ ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር አመርቂ አፈጻጸም መታየቱን አስረድቷል፡፡

በተለይ ለአርሶ አደሮች የተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ተጠቃሚዎቹ በችግኝ ተከላው በመሳተፍ  ለሚተክሏቸው ችግኞች ክትትል እንዲያደርጉ ከማስቻሉ ባለፈ በፍጥነት የሚደርሱ የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ  አግዟል፡፡

ነገር ግን አሁንም ችግኞቹ ከተተከሉ በኋላ በመንከባከብና ውሃ በማጠጣት የጽድቀት መጠናቸውን ለመጨመር ሰፊ ስራ የሚፈልግ በመሆኑ ለስኬቱ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ ነው፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ቴክኒካል ኮሚቴ ሪፖርት እንሚያሳየው በ2011 ዓ.ም ከተተከሉት 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች መካከል 83 ነጥብ 4 በመቶ  በ2012 ከተተከሉት 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ችግኞች መካከል 79 በመቶ መጽደቃቸውን ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡

በ2013 ዓ.ም 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን በአጠቃላይ ባለፉት አመታት በተደረገ የችግኝ እንክብካቤ አማካኝ ውጤት 80 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን የግብርና ሚኒስቴር ያወጣው ሪፖርት ያሳያል፡፡

ማጠቃለያ

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ስኬት አስተማማኝ እንዲሆን የተተከሉትን ችግኞች በባለቤትነት ማስተዳደርና መንከባከብ ያለበት የየአካባቢው ነዋሪ መሆን እንዳለበት ጥናት አቅራቢዎቹ አሳስበዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ለነዋሪዎቹ ማበረታቻ ማመቻቸት ወይም መስጠት፣ ዘላቂ የሆነ የገቢ ምንጭ እንዲፈጥሩበት እገዛ ማድረግና ተግባሩ በጋራ ባለቤትነት መቆጣጠር ተገቢ ነው፡፡

ይህንን አካባቢያዊ ባለቤትነት ማረጋገጥ ካልተቻለ የተተከሉትን ችግኞች የሚንከባከብና በባለቤትነት የሚያስተዳድር አካል ስለማይኖር ሁሉም በዘፈቀደ በመቁረጥና እድሜያቸውን በማሳጠር የአካባቢ ጥበቃ ጥረቱን ገደል ይከተዋል፡፡

አሁን ላይ ይህንኑ ተግባር ወደ መሬት ለማውረድ ጥረቶች የተጀመሩ ቢሆንም ልፋቱን ውጤታማ ለማድረግ በከፍተኛ ፍጥነት የባለቤትነት ስሜቱን በሁሉም ባለድርሻዎች ላይ ማጋባት ያስፈልጋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ የሚመራው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በመሆኑ ወጪውን የሚሸፍነው መንግስት ብቻ እንዲሆን አድርጎታል፣ ነገር ግን የአካባቢ ጥበቃ የሁሉንም አካላት የጋራ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ሀገር በቀልና አለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ለስኬቱ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡

መውጫ

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ 6 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የግብርና ሚኒስቴር ያስታወቀ ሲሆን በዚህም ከሚተከለው ችግኝ 60 በመቶው ለኢኮኖሚው አስተዋፅኦ የሚያደርጉ እና ከምግብ ዋስትና ጋር የተያያዙ ችግኞች ናቸው፡፡

ለችግኝ ተከላው በአገር አቀፍ ደረጃ ዝርዝር መርሐ ግብር እየተዘጋጀለት ሲሆን ባለፉት 3 ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ ሲተገበር የቆየው የአረንጓዴ አሻራ ጥሩ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡