ዘንድሮ በሲዳማ ክልል ከ314 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል

258

ሀዋሳ፣ ሰኔ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ከ314 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ነገ በይፋ የሚጀመረውን 4ኛ ዙር ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሃብትና አነስተኛ መስኖ ልማት ዳይሬክተር አቶ በረከት አሰፋ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

ለተከላ ከተዘጋጁ ችግኞች ውሰጥ 70 ከመቶ የሚሆኑት ለጥምር ደን እርሻ የሚሆኑ እንደ ፍራፍሬ፣ ቡናና ቀርከሃ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ለተከላው ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተለይቶ ከ200 ሚለዮን በላይ ጉድጓዶች መቆፈራቸውን ጠቁመው፤ ከሐምሌ 01 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እንደ ክልል ተከላው እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራ በህብረተሰቡ ዘንድ የስራ ባህል  እየሆነ መምጣቱን ገልጸው፤ ችግኝ አፍልተው ለገበያ የሚያቀርቡ በርካታ አርሶ አደሮች መፈጠራቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።  

ህብረተሰቡ በየዓመቱ ለተከላቸው ችግኞች  የሚያደርገው እንክብካቤ  መሻሻሉን ገልጸዋል።

በክልል ደረጃ በህዝብ ንቅናቄ በሚጀመረው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአንድ ጀምበር 20 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብሩ በክልሉ ባሉ 646 ንኡስ ተፋሰሶች ላይ እየተከናወነ ያለውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ውጤታማ እንዲሆን ያስቻለ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አበባየሁ ላሊማ በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ ዘንድሮ በሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ከተዘጋጀው ችግኝ 40 በመቶ የሚሆነው የፍራፍሬና የቡና ችግኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሀዋሳ ከተማ በተከለሉ አረንጓዴ ቦታዎች ያሉ የጥላ ዛፎቿን በቀጣይ በፍራፍሬ ዛፍ መቀየር የሚያስችል የፍራፍሬ ችግኝ ዝግጅት ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም