አሚኮ ህብረ ብሄራዊ አንድነት እንዲጎለብት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

182

ባህር ዳር፣  ሰኔ 13/2014 (ኢዜአ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ህብረ ብሄራዊ አንድነትና መከባበርን በፅኑ መሰረት ላይ ለመትከል የጀመረውን ስራ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስገነዘቡ።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን /አሚኮ/ ”አሚኮ ህብር” የሚል 2ኛ “ቻናል” የቴሌቪዥን ስርጭቱን በ10 ቋንቋዎች ይፋዊ የስርጭት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ዛሬ በባህርዳር ከተማ አካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ እንደገለጹት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሁለተኛ ቻናል መከፈት የሀገርን አንድነት ለስጋት የሚጥሉ የጥላቻ ንግግሮችንና የሀሰት ትርክቶች እንዲታረሙ ያግዛል።

“የበርካታ ቋንቋዎች፣ ዕምነት፣ ባህልና ስነ-ምህዳር ባለቤቶች የሆንን ኢትዮጵያዊያን እርስ በርስ ከሚያራርቁና ከሚያጋጩ ጉዳዮች ራሳችንን አርቀን ተደማምጠንና ተከባብረን በጋራ መኖር ይገባል” ብለዋል።

መከባበርን፣ መደማመጥንና አብሮነትን በፅኑ መሰረት ላይ ለመትከል ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝብ ማቅረብ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።

”አሚኮ ህብር” ቻናል ሚዛናዊ መረጃ፣ አብሮነትን፣ መከባበርን የሚያጎለብቱ መረጃዎችን ለህዝቡ ማድረስ እንደሚጠበቅበት ጠቅሰዋል።

ተቋሙ ዓለም አቀፍ ቴክኖሎጂን በመጠቀምና የበቃ የሰው ኃይል እንዲኖረው ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅበት የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ  ገልጸዋል።

”አሚኮ በህብረተሰቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ለክልሉ ህዝብ የልማት አለኝታ በመሆን ሲተጋ የቆየ ተቋም ነው” ያሉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ናቸው።

አሁን ባለንበት ወቅት ለሰላምና ለአብሮነት የሚሰሩ  ሚዲያዎች  የመኖራቸውን ያክል ለፅንፈኝነትና አክራሪነትና ኋላቀር አስተሳሰቦች በመጋለጣቸው ህብረተሰቡን ከሚያቀራርቡ ጉዳዮች ይልቅ በሚያራርቁ አጀንዳዎች የተጠመዱ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

እነዚህን ዕኩይ አጀንዳዎች በማጋለጥና ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ህብረተሰቡ ራሱ በራሱ እንዲወስን እያደረጉ ካሉ ሚዲያዎች መካከል አሚኮ ተጠቃሽ ሚዲያ ነው ብለዋል።

“በተለይ የለውጡ እንቅስቃሴ በአማራ ክልል እንዲቀጣጠል ከማድረግ ጀምሮ ለውጡ ፈር እንዲይዝ በማስቻል ለነበረው ሚና መንግስት የላቀ ምስጋና ያቀርባል” ብለዋል።

ሚዲያዎች አሁን ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመታጠቅ የመንግስት አጀንዳዎችንና ፍላጎቶችን ወደ ህዝቡ በማድረስ ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ሂደት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት ።

መገናኛ ብዙሃን ለዘላቂ ሰላምና ብልጽግናና ለህብረ ብሄራዊ አንድነት መጎልበት ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ለዚህም መገናኛ ብዙሃን ከተለምዶ አሰራር ተላቀው ህብረተሰቡ የደረሰበትን የንቃተ ህሊና የሚመጥን፣ የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክር፣ ሁለንተናዊ ዕድገትን የሚያጠናክሩ ዘገባዎችን ማቅረብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።  

ተቋማቸው ህብረ ብሄራዊ አንድነትንና ብዝሃ ልሳን ለመሆን ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም እየሰራ ይገኛል ያሉት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ ናቸው ።

ኮርፖሬሽኑ ላለፉት 27 ዓመታት በሚዲያ ዘርፉ የራሱን አሻራ እያሳረፈ የመጣ አዳጊ የሚዲያ ተቋም እንደሆነ ተናግረዋል።

በውስን ባለሙያዎች ስራ የጀመረው አሚኮ የቋንቋዎችን ቁጥር እያሳደገና የአገልግሎቱን ተደራሽነት እያሰፋ ህብረብሄራዊ አንድነትንና ወንድማማችነትን ለማስረፅ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ ውስጥ ከሚነገሩ ቋንቋዎች በተጨማሪ ሀገራዊ መስተጋብሩን ለማጠናከርና የተዘሩ የሀሰት ትርክቶችን ለማስተካከል ህብረብሄራዊ ወንድማማችነት ማጠናክር የሚያስችሉ የማስፋፊያ ስራዎችን በመስራት የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ለስርጭት ማብቃቱን ተናግረዋል።

በአዲሱ ጣቢያ ሁሉንም አቅሞች በመጠቀም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን መረጃ ለማድረስ ይሰራል ብለዋል።

በአዲሱ ”አሚኮ ህብር” ቻናል በአማርኛ፣ ህምጠኛ፣ በአፋርኛ፣ በትግርኛ፣ በእንግሊዘኛ፣ በአዊኛ፣ በኦሮሞኛ፣ በጉምዝኛ፡ በግዕዝና በአረበኛ ቋንቋዎች ከዛሬ ጀምሮ የስርጭት አገልግሎት ለህዝብ ተደራሽ ማድረጉን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በፕሮግራሙ የፌደራል፣ የተለያዩ ክልል ሃላፊዎችና የሚዲያ ዘርፍ አመራሮች ተገኝተዋል።