ቻይና ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር መረጋገጥ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች

152

ሰኔ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ቻይና ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር መረጋገጥ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል የቻይና አፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሹ ቢንግ ገለጹ።

የመጀመሪያው የቻይና እና የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ጉባዔ የቀንዱ አገራት እና የቻይና ልዑካን አባላት በተሳተፉበት ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ይህ ጉባኤ በአፍሪካ ቀንድ አገራት የሰላም፣ መልካም አስተዳደርና የልማት አጀንዳዎች ላይ ያተኩራል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በመድረኩ እንደገለጹት፤ ከ300 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያለው የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ለውጥ እና የሰው ሰራሽ ፈተናዎች የተጋረጡበት ቀጣና መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በውጭ ጣልቃገብነት፣ ግጭት፣ ድርቅ፣ የዓለም አቀፍ ሁነቶች ሳቢያ በተባባሰው የዋጋ ንረት የቀጣናው ህዝብ ለመልከ-ብዙ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እንደተዳረገ ተናግረዋል።

ይህም ሆኖ ግን ቀጣናው በተፈጥሮ ሃብትና በሰው ኃይል ረገድ ተስፋና ዕድሎች እንዳሉት ጠቁመዋል።

በመሆኑም የቀጣናው አገራት የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በመፍታት የቀጣናውን መጻኢ መዳረሻ መወሰን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ የቀጣናው አገራት ካለፉት ስህተቶች በመማር ለጉባኤው ውጤታማነት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ  አስረድተዋል።

አገራቱ ለጋራ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግ የሚመክሩበት ወቅት አሁን እንደሆነም አመላክተዋል።

የቀንዱ አገራት የሚፈትኗቸውን ችግሮች በውጭ ሃይሎች ድጋፍ ብቻ መቋቋም እንደማይችሉ ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ በጋራ በመቆም ለችግሮቻችው የመፍትሔ አካል መሆን እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ቀጣናው ወደመረጋጋትና ልማት ለማምጣት ህዝቡን ያሳተፈ ውይይት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዕውቀቶችን አቀናጅቶ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

የቀንዱ አገራት ኑሮ መሻሻል ከመንግስታት ባሻገር ሲቪል ማህበረሰቡ እና የንግድ ማህበረሰብም የራሱን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል።

አፍሪካ ቀንድ ህዝቦች በቋንቋ፣ ሃይማኖት እና በባህል የሚጋሯቸውን እሴቶች በመጠቀም በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ስትራቴጂካዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ስትራቴጂካዊ አጋር ከሆነችው ቻይና ጋር በቅንጅት እንደምትሰራ ገልጸዋል።

የቻይና በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ መልክተኛ አምባሳደር ሹ ቢንግ በበኩላችው ቻይና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ መልካም አስተዳደርና ልማት እንዲረጋገጥ በትብብር እንደምትሰራ ገልጸው፤ እስካሁንም በቀንዱ አገራት በልማት ረገድ ገንቢ ሚና ስለመጫወቷ አስታውሰዋል።

በቀጣይም ቻይና በቀናጠው አገራት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ ልማትና መልካም አስተዳደር እንዲረጋገጥ አጋርነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ከአፍሪካ ቀንድ አገራት በሰላምና ደህንነት የፖሊሲ ልምድ በመለዋወጥ አገራቱ  ልማት ላይ እንዲያተኩሩ ቻይና ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል፡፡

አገራቱ የሚያጋጥማችውን ውስጣዊ ልዩነቶች በውይይትና ምክክር እንዲሁም በአገር በቀል ፖለቲካዊ መፍትሄ አማራጮች ዕልባት ሊሰጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ሁሉን አቀፍ መልካም አስተዳደር የሰፈነበት ስርዓት መዘርጋት ለዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣናው ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳድር እንዲዘረጋ፣ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ፣ በቴክኖሎጂና ምርምር፣ በፕሮክቶች ፋይናንስ ድጋፍ እና በድህነት ቅነሳ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም እንዲሁ፡፡

በኢኮኖሚ ረገድ ዘላቂነት ያለው ቀጣናዊ ትስስርን ማጎልበት፣ ሽብርተኝነትን መከላከልና ኢንቨስትምንት እንዲስፋፋ ቻይና ድጋፏን እንደምታጠናክር ገልጸዋል።

በአገራቱ የተሰማሩ የቻይና ኩባንያዎች በማህበረሰብ አገልግሎት ሚናቸው እንዲጎለበት፣ አገራቱን በሚያስተሳስሩ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እንዘረጉ ተሳትፎ እንደምታጠናክርም ገልጸዋል።

የቀጣናው አገራት ከቻይና ጋር ያላቸው የንግድ ትስስር እንዲጨምር የነጻ ገበያን በማመቻቸት እና አገር በቀል ኢኮኖሚ ልማትን ስኬታማነት የመደገፍ ነባር አጋርነቷን እንደምታጠናክርም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ