መንግስት የጀመረው የህግ የበላይነትን የማስፈን ስራ በሽብር ቡድኖች ሴራ በፍጹም አይደናቀፍም!

76

ሰኔ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግስት በመላ ሃገሪቱ ሰላምን ለማስፈን የኢ-መደበኛ ታጣቂዎችንና በሽብር ቡድንነት የተፈረጁ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለመግታት ሁሉን አቀፍ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ይህ የመንግስትና የመላው ጸጥታ ሃይላችን የህግ የበላይነትን የማስከበር ተልእኮ ያነጣጠረበት የሸኔ የሽብር ቡድን እየደረሰበት የሚገኘውን ከፍተኛ ሽንፈት ለመሸፈን የጥፋት በትሩን ወደ ንጹሃን አዙሯል።

የሽብር ቡድኑ በቅርቡ በጋምቤላ፣ በደምቢዶሎና በጊምቢ ከተሞች ላይ የሰነዘራቸው የሽብር ጥቃቶች በጸጥታ ሃይሉ ቅንጅት ሲከሽፍ በበቀል የሽብር ተግባሩ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ በርካታ ንጹሃንን ህይወት በግፍ ቀጥፏል፣ ንብረትንም አውድሟል።

በሽብር ጥቃቱ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖችና ለደረሰው ጉዳት መንግስት የተሰማውን ልባዊ ሃዘን ይገልጻል።

ይህ ቡድን በንጹሃን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የቡድኑን ትክክለኛ ማንነት የሚያሳይ በመሆኑ የጥፋት ሃይሉ ሙሉ በሙሉ እንዲደመሰስ በመላው የክልልና የፌደራል የጸጥታ ሃይሎች የተጀመረው የተቀናጀ ተልእኮ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም