የፍትሕ ተቋማት ተገቢውን የአሰራር ማሻሻያ በማድረግ የሚነሳባቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታ ለመቅረፍ መሥራት አለባቸው

163

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2014 (ኢዜአ) የፍትሕ ተቋማት ተገቢውን የአሰራር ማሻሻያ በማድረግ የሚነሳባቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታ ለመቅረፍ መሥራት እንዳለባቸው የፌደራል ፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ገለጹ።

የፌደራል የፍትሕ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታና የሕዝብ እርካታ ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ አውደ- ጥናት በዛሬው እለት ተካሂዷል።

በመድረኩም ኢንስቲትዩቱ በፌደራል ፍርድ ቤቶች፣ በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና በማረሚያ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥና የሕዝብ እርካታን አስመልክቶ ያካሄደውን ጥናት ይፋ አድርጓል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የጥናቱ ዓላማ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ የሕብረተሰብ ቅሬታዎች እንዲፈቱ በጥናት ላይ የተመሰረተ የመፍትሔ ሀሳብ ማቅረብ መሆኑን ገልጸዋል።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በፍትሕ ተቋማት ግንባታ አበረታች ውጤት መመዝገቡ በጥናቱ መረጋገጡን ገልጸው፤ ነገር ግን ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ አሁንም ሕዝብን ለእንግልት የሚዳርጉ አሰራሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በተለይ የፍትሕ ተቋማት ከሕብረተሰቡ ፍላጎት እና እርካታ ጋር የሚጣጣም የአገልግሎት አሰጣጥ አስተሳሰብን በመገንባት ረገድ ክፍተት እንዳለባቸውም በጥናቱ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የፍትሕ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታዎችን ለመፍታት ተገቢውን የአሰራር ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

በኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ምትኩ መዳ በበኩላቸው፤ የፍትሕ ተቋማት ለውጭ ተገልጋዮች የሚሰጡት አገልግሎት ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ መሆኑን ጥናቱ ማመላከቱን ተናግረዋል።

ተቋማቱ የሕብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥ ጠንካራ የስነ-ምግባር ደንብ ሊኖራቸው እንደሚገባ በጥናቱ ምክረ-ሀሳብ ቀርቧል ነው ያሉት።

የተቋማቱ አገልግሎት ለብልሹ አሰራር እንዲጋለጥ ያደረጉ ሠራተኞች ላይ ተገቢ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም እንዲሁ።

ተቋማቱ በርካታ ሕብረተሰብ የሚገለገልባቸው በመሆናቸው ብልሹ አሰራሮችን ለማስተካከል በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።