በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር አርሶ አደሩን የሚጠቅሙ ችግኞች ተዘጋጅተዋል-ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ

104

ሆሳዕና፤ ሰኔ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዋቸሞ ዩኒቨርስቲ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ችግኞች ማዘጋጀቱን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ከተሰጠው የሰው ሃይል የማፍራት ተልዕኮ በተጨማሪ ሀገራዊ እድገትን ለማምጣት የተያዙ እቅዶች እንዲሳኩ በተለያዩ ተግባራት እየተሳተፈ ይገኛል።

ከእነዚህ የልማት ግቦች መካከል በአረንጓዴ አሻራው መርሐግብር ስኬት የሚያግዙ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንዲተከሉ ማድረግ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ1 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ማዘጋጀቱን እንደ አብነት አንስተዋል።

ለተከላ ከተዘጋጁ ችግኞች መካከል ቡናና ፍራፍሬዎች እንዲሁም ለአፈር ጥበቃ ጠቀሜታ ያላቸውና የአየር ንብረት ለውጥ ለመቆጣጠር የሚረዱ የተለያየ ዝሪያ ያላቸው ሀገር በቀል ችግኞች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲዉ ለተከላ ካዘጋጃቸው ችግኞች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚያከፋፍል ሲሆን ቀሪው ችግኞች ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢና ሌሎች ካምፓሶች ለመትከል ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።

በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና የአካባቢውን ህብረተሰብ በማሳተፍ ተከላዉ አንደሚከናወን ያሳወቁት ፕሬዚዳንቱ፤ ለችግኝ ተከላው ተገቢው ዝግጅት መጠናቀቁንም አስታውቀዋል።

የዩኒቨርሲቲዉ የምርምር ማዕከላት አስተባባሪ ዶክተር ዮሐንስ ኦራሞ በበኩላቸው የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለተከላ የሚሆን የተለያየ ዝርያ ያላቸው ችግኞችን የማዘጋጀት ቅድመ ዝግጅት ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አውስተዋል።

ባጠረ ጊዜ በመድረስ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚሰጡ ችግኞችን በማዘጋጀት አርሶ አደሩን የሚጠቅሙ እንደ የቡና፤ አፕል፤ አቮካዶና ማንጎ የመሳሰሉ ችግኞች በልዩ ትኩረት የተዘጋጁ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።

ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ጠቀሜታ ያላቸውና ከአከባቢው ስነ ምህዳር ጋር ቅርበት ያላቸው እንዲሁም የአየር ንብረትን የመቆጣጠርና የአፈር ለምነት የመጨመር አቅም ያላቸው እንደ ዋንዛ፤ ዝግባ፤ ኮሶ፤ ጥድ፤ ድግጣና መሰል ሀገር በቀል ተክሎችም ከተዘጋጁት መካከል ናቸው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባለፉት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች በሀዲያና ካምባታ ጣምባሮ ዞኖች በተራቆቱ መሬቶች ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞች የተከለ ሲሆን ባደረገው ክትትልም የጽድቀት መጠናቸው 85 በመቶ መሆኑን ማረጋገጡንም ዶክተር ዮሐንስ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ