ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ስኬት ኅብረተሰቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲረባረብ ተጠየቀ

122

አሶሳ፣ ሰኔ 13/2014(ኢዜአ) ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር ስኬት ህብረተሰቡ ተሳትፎውን አጠናከሮ እንዲቀጥል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ አሳሰቡ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ነገ ለሚጀመረው 4ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ነው።

ክልሉ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር ያደረገው ዝግጅት በፌዴራልና በክልሉ ከፍተኛ መንግሥት የስራ ኃላፊዎች ዛሬ በአሶሳ ዞን ኡራ ወረዳ ተጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ከተሳተፉት ከፍተኛ መንግሥት የስራ ኃላፊዎች መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ አንዱ ናቸው።

ዶክተር ቢቂላ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት በኅብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ በመርሃ ግብሩ በተከናወኑ ስራዎች ህዝቡ ተጠቃሚ እየሆነ መጥቷል።

በመሆኑም በዘንድሮው የክረምት ወራት ለሚካሄደው በ4ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር ስኬት ኅብረተሰቡ ተሳትፎውን በበለጠ አጠናክሮ  ለተገኘው ውጤት ቀጣይነት እንዲረባረብ ጠይቀዋል።

በአሶሳ ዞን ኡራ ወረዳ የጎበኙትን የአካባቢ ጥበቃ ስራና በአነስተኛ መስኖ የለማውን ሰብል ለአብነት አንስተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብሩን አጠናክሮ ማስቀጠል ኅብረተሰቡን በተግባር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን መመልከታቸውንም ዶክተር ቢቂላ ተናግረዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው ነገ ለሚጀመረው 4ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሉ 40 ሚሊዮን የተለያዩ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ችግኞቹ የሚተከሉበት የጉድጓድ ቁፋሮን ጨምሮ አስፈላጊው ዝግጀት በመጠናቀቅ ላይ ነው።

ለዘንድሮው መርሃ ግብር የተዘጋጁት ችግኞች የአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው እንደ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ዘይቱና፣ ቡና እና የብርቱካን የመሳሰሉ የፍራፍሬ ችግኞች ይገኙባቸዋል።

በክልሉ በስፋት የሚገኘው የቆላ ቀርከሃን ጨምሮ ሀገር በቀል ዛፎችም በችግኝ ዝግጅትና በተከላው ዋነኛ ትኩረት እንደተሰጣቸው አስረድተዋል።

ባለፉት ዓመታት ባከናወኑት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከሏቸው ችግኞች ደርሰው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ስራቸው የተጎበኘላቸው አርሶ አደሮች ገልጸዋል።

አንዳንድ የወረዳው አርሶ አደሮች በጉብኝቱ ለተሳተፉ አመራሮች እንዳስረዱት ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው ማገገም ችለዋል።

ቀደም ሲል በተለያየ ምክንያት የተጎዳው ስነምህዳር በተሰራው የተፈጥሮ ሀብትና የአካባቢ ጥበቃ አገግሞ የደን ሽፋን እያደገ መምጣቱን፣ ደርቀው የነበሩ ምንጮች መልሰው ማመንጨት መጀመራቸውን አስረድተዋል።

አርሶ አደሮቹ አክለውም መስኖን በስፋት በማካሄድ የተለያየ ሰብልና አትክልት በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በመስኖ አልምተው ተጠቃሚ ከሆኑበት ሰብል በቆሎን በአብነት ጠቅሰዋል።

በዚህም የስራ እድልም እንደፈጠረላቸውና የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ መቻላቸውን ጠቁመው “ከድህነት መላቀቅ ለመጀመራችን ማሳያ ነው” ሲሉም አስረድተዋል።