ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የችግኝና የመትከያ ቦታ ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የችግኝና የመትከያ ቦታ ዝግጅት ተጠናቋል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የችግኝና የመትከያ ቦታ ዝግጅት መጠናቀቁን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በነገው ዕለት እንደሚጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ትናንት ይፋ አድርገዋል።
ይህንን ተከትሎ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩ 6 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል የችግኝና የመትከያ ቦታ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በመንግሥት ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች፣ በማህበር በተደራጁ ወጣቶች እና በግለሰቦች የተዘጋጁ በቂ ችግኞች ለተከላ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ለችግኝ መትከልና ለመጽደቅ አመቺ በሆነ መሬት ላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውንም እንዲሁ።
የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በነገው ዕለት እንደሚያስጀምሩም ነው የገለጹት።
ሕብረተሰቡ እንደከዚህ ቀደሙ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩ በስፋት እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል።
ካለፉት ዓመታት የችግኝ ተከላ መርሃግብሮች በርካታ ትምህርት መገኘቱን ገልጸው፤ በተለይ ችግኝ በሚተከልበት ቦታ መምረጥ ላይ ጥሩ ልምድ መገኘቱን ተናግረዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት የተተከሉት ችግኞች አማካይ የጽድቀት ምጣኔ ከ80 በመቶ በላይ መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህ ዓመት እንደ አየር ንብረቱ ተስማሚ የሆነ ችግኝ ለመትከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ለደን ዛፍ፣ ለጥምር ደን እርሻ፣ ለምግብ የሚያገለግሉ፣ ለመኖ የሚውሉ እና የተለያዩ ሀገር በቀል ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ለአፈርና ውሃ ጥበቃ እርከን የተሰራባቸው ቦታዎች ላይ የሚተከሉ ችግኞች መኖራቸውንም ነው ያነሱት።
የችግኞች የጽድቀት ምጣኔ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመው፤ ሕብረተሰቡ በችግኝ ተከላና እንክብካቤም እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በየጊዜው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በተለይ አርሶ አደሩ በወል መሬት እና በተፋሰሶች አካባቢ ላይ በስፋት ችግኝ እየተከለና እየተንከባከበ ይገኛል ነው ያሉት።
በችግኞች እንክብካቤ ላይ አረም ማረምና ውሃ ማጠጣት ላይ በትኩረት በመሥራት የጽድቀት መጠኑን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ትናንት ባወጡት መግለጫ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከናወነ ዘመቻ ወደ 18 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
ይህንን ግብ ለማሳካትም በመላ ሀገሪቱ ከ20 ሚሊዮን ዜጎች በላይ ማሳተፍ እንደተቻለም ነው የተናገሩት።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለመትከል ከተዘጋጁ ችግኞች መካከል 52 በመቶ የሚሆኑት የግብርና እና የደን ዛፎች ሲሆኑ ከዚህ ውስጥ 47 በመቶዎቹ የደን ዛፎች ናቸው።
ቀሪዎቹ ደግሞ አካባቢን ለማስዋብ የሚውሉ ተክሎች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል።