ብሔራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ትክክለኛ አማራጭ ነው - የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

98

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ብሔራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ እየተፈጠሩ የሚገኙ አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ትክክለኛ አማራጭ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

መገናኛ ብዙኃን ብሔራዊ ምክክሩ ለሀገር ሁለንተናዊ ሰላም፣ ድህነትና ልማት የሚኖረውን ፋይዳ ለሕብረተሰቡ በሚገባ ማስገንዘብ እንዳለባቸው መክረዋል።

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ሚፍታህ መሀመድ፤ የተለያዩ አገራት የገጠሟቸውን ፖለቲካዊ ቀውሶች በምክክር መፍታታቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ብሔራዊ ምክክርም አሳታፊ ምህዳርን በመፍጠር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ትክክለኛ አማራጭ መሆኑን አንስተዋል፡፡

አገራዊ ምክክሩ የታቀደለትን ውጤት እንዲያስመዘግብ ደግሞ ባለድርሻ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በተለይ መገናኛ ብዙኃንና የሙያ ማህበራት ለምክክሩ ስኬት ከወዲሁ መሥራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ የፖለቲካ ልሂቃኑም ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት መሰረት የሚጥል ገንቢ ሚና መጫወት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር ሰለሞን ጓዴ፤ በኢትዮጵያ በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ደም አፋሳሽ ግጭት፣ መፈናቀልና ሞት እየተከሰተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እነዚህን ችግሮች በምክክር መፍታት ደግሞ  የተሻለና ተመራጭ መንገድ እንደሆነ ተናግረዋል።

በመሆኑም አገራዊ ምክክሩን በውጤታማነት በማከናወን ለሀገር የሚበጅ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት መምህሩ አብዶ ኢሎ፤ የበለጸጉ ሀገራት ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የሚያስችል ምክክርን አካሂደው ችግሮቻቸውን በማለፍ ከዕድገት ማማ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሚካሄደው ብሔራዊ ምክክር ግቡን እንዲመታ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ተሞክሮ መውሰድ እንደሚያሻም ጠቁመዋል፡፡

ብሔራዊ ምክክሩም የፖለቲካ ቅራኔ ያላቸው አካላትን በማቀራረብ ለችግሮች የጋራ መፍትሔ እንዲያበጁ ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡

መገናኛ ብዙኃን ብሔራዊ ምክክሩ ያለው ፋይዳ ላይ ተግባቦትን በመፍጠር ለስኬቱ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም