ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቆመን በመታገል ጠላቶቻችንን እናሸንፋለን -አቶ ሽመልስ አብዲሳ

171

ሚዛን አማን፣ ሰኔ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቆመን በመታገል ለውጡን ለመቀልበስ እየሰሩ ያሉ ጠላቶቻችንን እናሸንፋለን ሲሉ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሺመልስ አብዲሳ አስታወቁ።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ100 ሚሊሊዮን ብር ድጋፍ ዛሬ አበርክቷል።

ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በወቅቱ እንዳሉት ኢትዮጵያ ብዙ የማደግ ዕድሎች እንዳሏት ሁሉ በርካታ ፈተናዎች እየተጋረጡባት ነው።

“በጎ ነገር ሲሰራ ፈተናዎች በዙርያው ይበዛሉ” ያሉት አቶ ሽመልስ አብዲሳ “ከብልጽግና ሊገታን የሚሞክር ማንኛውንም ፈተና በጽናት ታግለን እናሸንፋለን” ብለዋል።

እንደ ክልል ሰላምና የልማት ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን  አስታውቀዋል።

“ለማንም የማያዝኑና የማይጨነቁ የክፋት ምንጭ የሆኑ ቡድኖች የህግ የበላይነት የማስከበር ሥራ ሲሰራ በጀመሩት ሽሽት በንጹሃን ላይ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት እየፈጸሙ” ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ቡድኖቹ በህጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያን ላይ የሽንፈት ጥቃት እያደረሱ እንዳለ ጠቁመው የክልሉ መንግስት ይህንን ፈተና ከህዝቡ ጋር ሆኖ በጽናት በመታገል  እንደሚያሸንፍ አረጋግጠዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት የጠላትን ሴራ ለማክሸፍ ወደ ኋላ ማፈግፈግ ሳያስፈልግ ችግሮችን እየተጋፈጡ በአንድነት መታገል ያስፈልጋል።

“ኢትዮጵያን አሸንፋለሁ ብሎ የሚያስብ ጠላት ህልሙ አይሳካም፤ ኢትዮጵያ ግን ድል ተቀዳጅታ ብልጽግናዋ እውን እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም” ሲሉ በአጽኖት ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከጎረቤት ክልሎች ጋር በመተባበር ሀገራዊ ፈተናዎችን ለመሻገር እንደሚሰሩ የገለጹ ሲሆን ዛሬ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ቦንጋ ከተማ በመገኘት አበርክተዋል።

በኢትዮጵያ 11ኛው ክልል ሆኖ አዲስ የተመሰረተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በአቅም እየደረጀ እንዲሄድ ክልሉ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ርእሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታውቀዋል።