ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ከ15 ሺህ በላይ መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት አበረከተ

104

ሰኔ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ከ15 ሺህ በላይ መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ዛሬ አበርክቷል።

"ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በሚከናወነው የመጻሕፍት ማሰባሰብ ንቅናቄ የተለያዩ ተቋማትና ዜጎች ሚናቸውን እየተወጡ ነው።

የሰላሌ ዩኒቨርሲቲም 15 ሺህ መጻሕፍትን በዛሬው ዕለት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አበርክቷል።መጻሕፍቱን የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር እሸቱ ወንድሙ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ተወካይ ዶክተር ታምራት ሃይሌ አስረክበዋል፡፡

ዶክተር እሸቱ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ መጻሕፍቱ በጤና፣ በህዋ ሳይንስ፣ በምህንድስና እንዲሁም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ናቸው።

ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታየ ደንደአ በግላቸው በኦሮምኛ ቋንቋ ያሳተሙትን የሰዋሰውና የተረት ይዘት ያላቸው 50 መጻሕፍትን ለአብርሆት አበርክተዋል፡፡

መጻሕፍቱ ሀገር በቀል እውቀትን ለማስፋፋትና በኦሮምኛ ቋንቋ ተረቶችና ሰዋሰው ላይ ለሚመራመሩና ለሚማሩ አጋዥ ሆነው እንደሚያገለግሉ ጠቅሰዋል።

መጻሕፍቱን የተረከቡት የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ተወካይ ዶክተር ታምራት ሃይሌ፤ ለአብርሆት ቤተመጻሕፍት እየተደረገ ያለው የመጻሕፍት ማሰባሰብ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በዛሬው እለት ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ላበረከታቸው መጻሕፍትም ምስጋና አቅርበው በቀጣይም ሌሎች ዜጎችና ተቋማት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ከታህሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን ሚያዚያ 28 ቀን 2014 ዓ.ም የተጀመረው መጻሕፍት የማሰባሰብ ሥራውም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

አብርሆት ቤተ-መጻሕፍት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጻሕፍት የመያዝ አቅም እንዳለው ተነግሯል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም