ከ100 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ

223

ደሴ፤ ሰኔ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን በበጀት ዓመቱ ከ100 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ የተገነቡ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን የዞኑ ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የመሰረተ ልማት ተወካይ ቡድን መሪ አቶ ወርቅነህ ሽፋው ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በፈጸመው ወረራ በዞኑ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል፡፡

የህብረተሰቡ የዘመናት ጥያቄ የነበሩ አዳዲስ መሰረተ ልማቶችም እንዳይሰሩ ከፍተኛ መሰናክል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

አቶ ወርቅነህ  እንዳሉት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተደረገው ርብርብ ከ100 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ ተችሏል።

ከተሰሩ መሰረተ ልማቶች መካከል 35 ኪሎ ሜትር ጠጠር መንገድ፣ 5 ኪሎ ሜትር ካናል፣ 32 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድ ከፈታ፣ 17 አነስተኛ ድልድዮች፣ 30 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ 11 የውሃ ቦኖ ግንባታና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች ይገኙበታል፡፡

ለመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ ህብረተሰቡ 27 ሚሊዮን ብር ቁሳቁስ በማቅረብና በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው ቀሪው ወጪ በመንግስትና በዓለም ባንክ በጀት የተሸፈነ መሆኑን አብራርተዋል።

የመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ የተከናወኑት በ9 ከተማ አስተዳደሮችና በ15 መሪ ማዘጋጃ ቤት ከተሞች መሆኑን ገልጸዋል።

የመሰረተ ልማቶቹ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ህብረተሰቡ መጠበቅና ሲበላሹ ፈጥኖ መጠገን ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡

አቀስታ፣ ደጎሎ፤ ቱሉአውሊያ፣ ከላላ፣ ሐይቅና መካነሰላም ከተሞች የተሻለ ስራ የተከናወነባቸው ከተሞች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የአቀስታ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ብርሃኑ ሽመልስ በበኩላቸው ከ7 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጭ 3 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድና ሁለት የውኃ መፋሰሻ ካናሎችና ሌሎችን ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ስራው ውጤታማ እንዲሆን ህብረተሰቡ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

የከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ብርቱካን መሃመድ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው የውሃ መፋሰሻ ካናል ባለመኖሩ በየአመቱ በጎርፍ ይጠቁ እንደነበር ጠቅሰው የተገነባው ካናል ችግሩን እንዲሚያስቀርላቸው ተናግረዋል።

በቀጣይም ከአመራሩ ጋር በመቀናጀት የአከባቢያቸውን ልማት ለማፋጠን እንደሚሰሩ ገልጸዋል ፡፡

''በከተማችን የተሰራልን የኮብልስቶን መንገድ በክረምት በጭቃ፣ በበጋ ደግሞ በአቧራ የነበረብንን ችግር ቀርፎልናል'' ያሉት የሐይቅ ከተማ ነዋሪ አቶ አህመድ ያሲን ናቸው፡፡

መሰረተ ልማቶች ሲሰሩ በጉልበትና በገንዘብ መሳተፋቸውን የገለጹት አቶ አህመድ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡም ተገቢውን ጥበቃ እናደርጋለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም