ሚኒስቴሩ ዲጂታል የመረጃ አስተዳደር ስርዓት መዘርጋቱን አስታወቀ

90

አዳማ፤ ሰኔ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ወቅታዊ መረጃዎችን አደራጅቶ ለመያዝ የሚያስችል ዲጂታል የመረጃ አስተዳደር ስርዓት መዘርጋቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ በራሱ ያበለፀጋቸውን የዲጂታል መረጃ አስተዳደር ስርዓት ማስተዋወቂያ መድረክ በአዳማ አካሂዷል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት "የማህበራዊ ጥበቃ ስራን ውጤታማ ለማድረግ በአግባቡ የተደራጀ የመረጃ አስተዳደር ስርዓት ሊኖረን ይገባል"።

የመረጃ አስተዳደር ስርዓቱ በተለይ በማህበራዊ ጥበቃ ስር የተለያዩ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ስራን በተገቢው አደራጅቶ ለመያዝ የሚያስችል ዲጂታል አሰራር መሆኑንም ገልፀዋል።

ይህ የዲጂታል የመረጃ አስተዳደር ስርዓቱ የከተሞች ልዩ ድጋፍ ተጠቃሚዎች ሥርዓት፣ የአረጋውያንና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መረጃን አደረጅቶ ለመያዝ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

ነባሩ የመረጃ አያያዝ ኋላቀር በመሆኑ ከክልሎች፣ ከተሞች እንዲሁም ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በማግኘት ረገድ ሰፊ ክፍተት ያለበት መሆኑን ተናግረዋል።

አዲሱ ዲጂታል የመረጃ ስርዓት በተቋሙ የውስጥ አቅም የለማና ለአገልግሎት የበቃ መሆኑንም ገልጸዋል።

እየተደገፉ አነስተኛ ስራ ለሚሰሩት አረጋዊያን የታለመና የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት የመረጃ አስተዳደር ስርዓት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተደግፈው እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዘመናዊ የመረጃ ስርዓቱ ከፌዴራል እስከ ክልልና ከተሞች እንዲሁም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚገለገሉበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ ዲጂታል የአረጋውያን የመረጃ አስተዳደር ስርዓት መዘጋጀቱን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታዋ ቀድሞ የነበረው የአረጋውያን የመረጃ አያያዝ ሙሉ በሙሉ በወረቀት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ክፍተት የነበረበት መሆኑን ተናግረዋል።

የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዲጂታል የመረጃ አያያዝ ስርዓት መዘጋጀቱን ገልፀው፣ ዲጂታል የመረጃ ስርዓቱ በተለይ የተቀናጀ ድጋፍ ለማድረግ እንዲቻል ጭምር ቁልፍ አጋዥ እንደሆነም ተናግረዋል።

አዲስ ወደ ስራ ለማስገባት የለማው ዲጂታል የመረጃ ስርዓቱ በተሟላ መልኩ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ በመድረኩ ላይ ጽሑፍ ያቀረቡት በሚኒስቴሩ የማህበራዊ ዘርፍ ቴክኒክ አማካሪ አቶ ወንድወሰን ኤልሳ ናቸው።

በተለይ የተለያዩ የድጋፍና ዕገዛ ፕሮግራሞችና ፕሮጄክቶች በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርተው መስራት የተዘጋጀው ዲጂታል የመረጃ አያያዝ ስርዓቱ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት ፋይዳው የጎላ እንደሆነም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም