የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት በተቀናጀ የዲጂታል ሚዲያ መደገፍ ያስፈልጋል

83

ሰኔ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት በተቀናጀ የዲጂታል ሚዲያ መደገፍ እንደሚያስፈልግ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ተናገሩ።

ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ የብልጽግና ፓርቲ አመራር እና የህዝብ ግንኙት ባለሙያዎች የዲጂታል ሚዲያ ስልጠና ዛሬ በስራ አመራር ማሰልጠኛ ተቋም እየተሰጠ ነው።

ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በወቅቱ እንዳሉት በኢትዮጵያ ባለፉት አራት አመታት ለውጥ ተመዝግቧል።

በአንፃሩ የጥፋት ቡድኖች ከፍተኛ የትርክት ወሬ በማዛመት ለውጡን ለማደናቀፍ ዘመቻ ከፍተዋል።

በተለይም የብሄር ብሄረሰቦች እና የኢትዮጵያውያን አይን በሆነው የህዳሴው ግድብ መገኛ የሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ ትርክቱ ዋነኛ ትኩረት ማድረጉን አመልክተዋል።

በለውጡ አመታት ኮሚኒኬሽኑን ለማጠናከር የተጀመረ ጥረት ቢኖርም በሚፈለገው ልክ እንዳልሆነ ዶክተር ቢቂላ አመልክተዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶችን በተደራጀ ዲጂታል ሚድያ መደገፍ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገው አስታውቀዋል።

ለዚህ ደግሞ ፌደራል ከክልል እንዲሁም ክልል ከክልል የተናበበ በዜጎች መካከል ፍቅርና አንድነትን በማጠናከር የሃሰት ትርክቶችን የሚመክት የመረጃ ስርጭት መጠናከር አለበት ነው ያሉት።

ህብረተሰቡን ከድህነት ለማላቀቅ በተሠሩ ስራዎች ልክ የፓርቲው አመራሮችም ሆኑ ውጤቶቹን በመረጃ አስደግፈው ማሳየት እንደሚሻ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው ክልሉ ለኮሚኒኬሽን ልማት ልዩ ትኩረት መስጠቱን ገልፀዋል።

በ160 ሚሊየን ብር ወጪ በቅርቡ ስርጭት የሚጀምረውን የክልሉን ቴሌቭዥን ጣቢያ በአብነት በመጥቀስ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም