ስደተኞችንና ተፈናቃዮችን ያማከለ የፖሊሲ ማዕቀፍ በማዘጋጀት አኮኖሚያዊ ለውጦችን ማከናወን ያስፈልጋል-የአለም ጤና ድርጅት

301

ሰኔ 13 ቀን 2014(ኢዜአ) ስደተኞችንና ተፈናቃዮችን ማዕከል ያደረገ የፖሊሲ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ለሁለንተናዊ እድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መስራት እንደሚገባ የአለም ጤና ድርጅት አስገነዘበ።

የስደተኞች ቀንን አስመልክቶ የአለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት በጦርነት፣ በግጭት፣ በሰብአዊ መብት ጥሰትና በሌሎች አስገዳጅ ምክንያቶች በአለም አቀፍ ደረጃ ከ100 ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች መፈናቀላቸውንና መሰደዳቸውን ገልጿል።

ሰዎች ከአካባቢያቸው በአስገዳጅ ሁኔታ በመውጣታቸው የተነሳ አሳሳቢ ለሆኑ የአካልና የአእምሮ ህመም መዳረጋቸውንም ነው የአለም ጤና ድርጅት የገለጸው።

በአሁኑ ወቅት ለስደትና መፈናቀል እየዳረጉ የሚገኙ ጦርነቶችና አስገዳጅ ሁኔታዎች በጊዜ መፍትሄ ካልተሰጣቸውም ለከፋ ድህነትና አለመረጋጋት እንደሚዳርጉ አሳስቧል።

አክሎም ሰዎች በሚያጋጥማቸው መፈናቀልና ስደት የተነሳ ጥብቅ አካባቢዎች ለማህበራዊ ኑሮ አገልግሎት በማዋላቸው በረሃማነት የመስፋፋት ሁኔታው ከፍተኛ መሆኑን አመልክቷል።

በስደትና መፈናቀል ውስጥ ያሉትን ሰዎች ያማከለ የፖሊሲ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ለሁለንተናዊ እድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መስራት ይገባል ሲልም የመፍትሔ አቅጣጫ ጠቁሟል።

የስደተኞችንና ተፈናቃዮችን የጤና ሁኔታ፣ የኢኮኖሚ እንዲሁም ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚያበረታቱ ፖሊሲዎች በሥራ ላይ ከዋሉ ስደተኞች በሀገር የኢኮኖሚ ብልጽግና ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ገልጿል።