የአማራና የአፋር ክልሎች አመራሮች ለዘላቂ ልማትና ብልፅግና በትብብር እንደሚሰሩ አስታወቁ

156

ደሴ፣ ሰኔ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአማራና የአፋር ክልል አመራሮች አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ዘላቂ ልማትና ብልፅግና ለማረጋገጥ በትብብር እንደሚሰሩ አስታወቁ።

በክልሎቹ መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር ያለመ የአመራሮች ውይይት ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል።

የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንደገለጹት፤ በባህል ተሳስረው፣ ተዋልደውና ተዛምደው የኖሩና የሚኖሩ ህዝቦችን ለማጋጨት የሚሰሩ የጥፋት ቡድኖች አሉ።

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በግጦሽ ሳር፣ በውሃና በሌሎች ጥቃቅን ጉዳዮች አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ የብሔርና የእምነት በማስመሰል የጥፋት ተልዕኳቸው ለማሳካት አሁንም እየባዘኑ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ የክልሎቹ አመራር በየደረጃው ተቀራርቦና ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ችግሮችን ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን በመፍታት አንድነትንና ሰላምን እያጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።

የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን እስከ ቀበሌ ድረስ በማጠናከር ልማትና ብልጽግናን እውን በማድረግ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የአፋር ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ሁመድ በበኩላቸው የአፋርና የአማራ ህዝቦች በበርካታ ባህልና እሴቶች ከመመሳሰላቸው ባሻገር ፈጽሞ የማይለያዩ፣ በደም የተሳሰሩ ወንድማማችና እህትማማች ናቸው ብለዋል።

በህዝቡ መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚሰሩ ቡድኖች ቢኖሩም በህዝቡ አርቆ አሳቢነት ሴራው እየከሸፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አለመግባባቶች ካጋጠሙ የሁለቱ ክልሎች አመራር ተቀናጅቶ በመስራት መፍትሄ እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ ህዝቡ አንድነቱን ጠብቆ ልማቱን እንደሚያረጋግጥ ተናግረዋል።

”አንድነታችንን፣ ሰላማችን በማይፈልጉና በመካከላችን ጭምር ባሉ የጥፋት ኃይሎች አንበረከክም” ያሉት የአፋር ክልል ዞን አምስት ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓሊ ማቴ፤ ዞኑን ከሚያዋስኑት ሰሜን ሸዋ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብና ደቡብ ወሎ ዞኖች ጋር በመቀናጀት በርካታ ትንኮሳዎችን ማክሸፍ መቻሉን ገልጸዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው በአዋሳኝ አካባቢ የጋራ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባትና የህዝቡን ግንኑነት ለማጠናከርም ጅምር ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

“የኮሙኒኬሽን ችግሮችና ግጭት” በሚል ርዕስ ለመድረኩ ጽሁፍ ያቀረቡት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሚድያና የኮሙኒኬሽን መምህር አቶ አየለ አናውጤ እንዳሉት፤ በግለሰቦች የሚፈጠሩ ጥቃቅን አለመግባባቶች በወቅቱ መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል።

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ ባደረጉት ጥናት የማይለያዩ፣ የተሳሰሩ፣ የተዋለዱና በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብራቸውም ተመሳሳይ መሆኑን ማረጋገጣቸው ጠቅሰው፤ ሁለቱን ሕዝቦች አጋጭተው ትርፍ የሚፈልጉ መኖራቸውን የጥናታቸው ግኝት ማረጋገጥ እንደቻሉም ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ