አብን ዶክተር በለጠ ሞላ ከፓርቲው ሊቀመንበርነት ለመነሣት ያቀረቡትን ጥያቄ ሳይቀበለው ቀረ

243

ሰኔ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ ሊቀመንበር ዶክተር በለጠ ሞላ ከሃላፊነት ለመነሳት ያቀረቡትን ጥያቄ የፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴ ሳይቀበለው ቀረ።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባውን በአዲስ አበባ አካሂዷል።

የማዕከላዊ ኮሚቴውን አስቸኳይ ስብሰባ በማስመልከት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ጣሂር መሀመድ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የፓርቲው ሊቀ መንበር ዶክተር በለጠ ሞላ ከፓርቲው ሃላፊነት ለመነሳት ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቅሰው፤ማእከላዊ ኮሚቴው ጥያቄያቸውን ሳይቀበለው መቅረቱን ተናግረዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት ፓርቲውን በስራ አስፈጻሚነት ሲመሩ የነበሩ ሌሎች ስራ አስፈጻሚዎችም ከቦታቸው ለመልቀቅ ሀሳብ ማቅረባቸውን ጠቁመው በማእከላዊ ኮሚቴው ተቀባይነት አላገኘም ብለዋል።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ጉዳዩን በጥልቀት ከተወያየ በኋላ ሃላፊዎቹ ያቀረቡትን ጥያቄ ሳይቀበለው መቅረቱን አብራርተዋል።

ሐምሌ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን በማድረግ ፓርቲውን የሚመሩ አመራሮችን ለመምረጥ መወሰኑንም ተናግረዋል።

"በሌላ በኩል ፓርቲው እውቅና ያልሰጣቸው አካላት ጉባኤ እናካሂዳለን በሚል እየተንቀሳቀሱ ነው" ያሉት አቶ ጣሂር፤ይህ ከፓርቲው እውቅና ውጪ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም