በአዲስ አበባ የህዝባዊ ሰራዊት አደረጃጀት እውን ከሆነ በኋላ በወንጀል መከላከል የተመዘገበው ውጤት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት

ሰኔ 12/2014/ኢዜአ/ በመዲናዋ የህዝባዊ ሰራዊት አደረጃጀት እውን ከሆነ በኋላ በወንጀል መከላከል የተመዘገበው ውጤት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ለመዲናዋ ሠላምና ደህንነት መረጋገጥ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ህዝባዊ ሰራዊት እውቅና ተሰጥቷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ እና የሰላምና የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀንዓ ያደታ ተገኝተዋል።     

በዕለቱም የክፍለ ከተሞች ህዝባዊ ሰራዊት፣ የክፍለ ከተማ አስተዳደሮች፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና የመዲናዋ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን እውቅና ከተሰጣቸው መካከል ናቸው።

እውቅናው በተለይም በህግ ማስከበር ወቅት፣ ደረቅ ወንጀልን በመከላከልና የአካባቢ ሠላምና ጸጥታ ላይ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ለማመስገን ያለመ መሆኑም ነው የተጠቀሰው።   

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልእክታቸው "አዲስ አበባ የሠላም እንዲሁም የአብሮነትና የአንድነት ከተማ የሆነችው በእናንተ ጥረት ነው፤ ልትመሰገኑ ይገባል" ብለዋል።    

ብርድና ጭለማ ሳይበግራችሁ ወኔን ታጥቃችሁ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት ለከተማዋ ሠላም መረጋገጥ የሰራችሁት ሥራ ከአዲስ አበባ ባለፈ አገር ያኮራ ተግባር ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በሰላሙ ላይ የተገኘው ውጤት ከተባበርንና በጋራ ከቆምን የማንሻገረው ችግር የማናልፈው ፈተና እንደሌለ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።    

"በኢኮኖሚ ማደግን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ብዙ ውጥኖች አሉን" ያሉት ከንቲባዋ ውጥኖቹ እንዲሳኩ የሠላም መረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነም አብራርተዋል።   

ህዝባዊ ሰራዊቱ ለሰላም ዘብ ከመቆም ጎን ለጎንም በልማትም ላይ መሳተፍ እንዳለበት ያመለከቱት ከንቲባ አዳነች በአረንጓዴ አሻራ፣በቤት እድሳትና በበጎ አድራጎት ስራዎችም ተሳትፏቸው እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል።    

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀንዓ ያደታ፤ በከተማዋ የህዝባዊ ሰራዊት አደረጃጀት ከተዘረጋ በኋላ በወንጀል መከላከል የተሻለ ውጤት መታየቱን ገልጸዋል።  

የህገ ወጥ ጦር መሳሪያዎች፣ ኮንትሮባንድ፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ በርካታ ወንጀሎችን መከላከል እንደተቻለም አስረድተዋል።   

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ተቋማዊ አደረጃጀቶችን እያጠናከረ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ቀንዓ የተለያዩ ደንቦች፣ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች መዘጋጀቱንም አክለዋል።

እውቅና የተሰጣቸው ህዝባዊ ሰራዊት ብርጌድ አመራሮች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እውቅናው በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።    

በሠላምና ደህንነት ላይ የጀመርናቸውን ተግባራትንም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።  

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ህዝባዊ ሰራዊት ብርጌድ መሪ አቶ ጸጋዬ ባርክልኝ ሠላምና ጸጥታው ላይ የበለጠ ለመስራት ቃል የገባንበት ቀን ነው ሲሉ ተናግረዋል።   

የጉሌሌ ክፍለ ከተማ ህዝባዊ ሰራዊት ብርጌድ አመራር አቶ ፍሬው በኃይሉ "ለሰራነው ስራ እውቅና ማግኘታችን የሚያስደስት ነው፤ በቀጣይ ለምንሰራውም አደራም ጭምር ነው" ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም