በህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት በትኩረት ይሰራል-ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

349

ሰኔ 12 ቀን 2014(ኢዜአ) በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ከሶሰት ዓመታት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት እየተሠራ መሆኑን የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

31ኛው አገር አቀፍ የአፍሪካ ህጻናት ቀን በአሶሳ ተከብሯል።

በአከባበሩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህጻናት መብትና ደህንነት ቻርተርን የራሷ የህግ አካል ሆኖ እንዲጸድቅ ማድረጓን አስታውሰዋል፡፡

ቻርተሩ በህጻናት ህይወትና አካል ላይ የሚደርስ ማንኛውንም ጉዳት ወንጀል አድርጎ እንደሚደነግግም አስረድተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በተለይም የሴት ልጅ ግርዛት እና ያለእድሜ ጋብቻን በፈረንጆቹ 2025 ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት እየሠራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠትና የማህበረሰብ ንቅናቄ በማካሄድ ግንዛቤ መፍጠር ሚኒስቴሩ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ቀላል በማይባሉ የሃገሪቱ ቀበሌዎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማስቆም መቻሉን ዶክተር ኤርጎጌ ለአብነት አንስተዋል፡፡

ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የተቀናጀ ስራ እንደሚጠይቅም አሳስበዋል፡፡

ህጻናት የነገ ሃገር ተረካቢ መሆናቸውን ማህበረሰቡ በሚገባ ተገንዝቦ ለነገ ዛሬ መስራት እንዳለበትም ሚኒሰትሯ አስገንዝዋል፡፡

"ህጻናት ሠላምን አጥብቀው ይፈልጋሉ" ያሉት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ናቸው፡፡

May be an image of 1 person and indoor

በሰላማዊ አካባቢ የሚያድጉ ህጻናት ብሩህ አእምሮ እንደሚኖራቸው ሁሉ ሠላም በሌለበት የሚኖሩ ደግሞ ስነልቦናቸው እንደሚጎዳ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል፡፡

"የምንመኛትን የለማች ኢትዮጵያን አውን የምናደርገው ዛሬ ህጻናት ላይ በምንሠራውና በምናስመዘግበው ተጨባጭ ውጤት ነው" ብለዋል፡፡

በመሆኑም የተስፋችን ነጻብራቅ በሆኑ ህጻናት ላይ መልካም አሻራን ጥሎ ለማለፍ በየደረጃው የምንገኝ አመራሮች ትኩረት ሰጥተን መስራት የግድ ይለናል ሲሉ አቶ አሻድሊ ተናግረዋል፡፡

" የክልላችን መንግስት ነገ የምናያት የበለጸገች ኢትዮጵያ አውን መሆን የምትችለው ዛሬ ህጻናት ላይ በምንሠራው የላቀ ስራ እንደሆነ አጥብቆ ያምናል" ብለዋል፡፡

የተስፋ ነጸብራቅ በሆኑ ህጻናት ላይ መልካም አሻራዎችን ጥሎ ለማለፍ በሚሰሩ ስራዎች ሁሉ በየደረጃው ያሉ አመራር አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህጻናት ፓርላማ አፈ ጉባኤ ህጻን ቅዱስ ሞላ በበኩሉ በኢትዮጵያ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆም የሚወሰዱ እርምጃዎች በፖሊሲ ማዕቀፍና ተቋማዊ አደረጃጀት ጭምር ምላሽ እየተሰጣቸው መሆኑ የሚበረታታ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

May be an image of 1 person, standing and indoor

በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ፣የህገ ወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑና የትምህርት እድል ያላገኙ ህጻናትን በመታደግ ረገድ ግን ብዙ መሰራት እንዳለበት ነው ያመለከተው፡፡

በዚሁ ወቅት የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች ለተጎዱ ህጻናት ድጋፍ የሚውል የ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

ክልሎች ለህጻናት ደህንነት መጠበቅ ላበረከረቱት አስተዋፀኦ የእውቅና ሽልማት ያገኙ ሲሆን በዝግጅቱ ማጠቃለያ ላይ ደግሞ የችግኝ ተከላም ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም