መገናኛ ብዙሃን ህዝብና አገርን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ዘገባዎች ሙሉ በሙሉ መውጣት አለባቸው

ሰኔ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ)መገናኛ ብዙሃን ህዝብና ሀገርን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ዘገባዎች ሙሉ በሙሉ እንዲወጡ ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያካሄድ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ምስረታ ጠቅላላ ጉባኤ ትናንት በደሴ ተካሂዷል፡፡

በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የፍቃድና ምዝገባ ዳይሬክተር አቶ ፈንታሁን አስረስ ለኢዜአ እንደገለጹት መገናኛ ብዙሃን ከተቋቋሙበት ዓላማ ጎን ለጎን ለህዝብ አንድነትና ሰላም መስራት ግዴታቸው ነው፡፡

ይሁን እንጂ የተወሰኑ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ጭምር ከዚህ በፊት ከህግና መመሪያ ውጭ ህዝብና ሀገርን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ የጥላቻ፣ የልዩነት፣ለሁከትና ብጥብጥ ሊዳርጉ የሚችሉ ዘገባዎችን ሲዘግቡ ተስተውለዋል ብለዋል፡፡

የሀገርና የህዝብን አንድነትና ዘላቂ ሰላም ለመጠበቅ ሲባል ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ባደረገው ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ብዙዎች መሻሻል አሳይተዋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ሙሉ በሙሉ ከችግራቸው እንዲላቀቁም በየደረጃው የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው፤ በራሳቸው እንዲዳኙም የሚድያ ካውንስል ተቋቁሟል፤ በቅርቡ ወደ ስራ እንዲገባ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

አሁንም የሚሰሯቸውን ፕሮግራሞችና ዘገባዎች በመከታተል ከስህተታቸው እንዲማሩ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን መንግስትና ህዝብ ተረጋግቶ ወደ ልማት እንዳይገባ ከሚያደርጉና ከግጭት አቀጣጣይ ጉዳዮች እንዲጠነቀቁም ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

ጋዜጠኞችም የሙያ ስነ ምግባራቸውን ከመጠበቅ ባለፈ ሀገርና ህዝባቸውን በማሰብ በሃላፊነትና ከስሜት ነጻ ሆነው ለሰላም፤ለአንድነትና ለልማት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

መመዘኛውን ለሚያሟሉ መገናኛ ብዙሃን ፍቃድ እየተሰጠ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አቀፍ ሬዲዮ ጣቢያም አብዛኛውን መመዘኛ በማሟላቱ ፍቃድ ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ጣቢያው ፍቃዱን ባገኘ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ስርጭት ካልጀመረ ፍቃዱ እንደሚሰረዝ ያሳሰቡት ዳይሬክተሩ ለአካባቢው ህዝብ አብሮነት፣ ለሰላምና ልማት መስራት እንዳለበትም አስገንዘበዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ በበኩላቸው ጣቢያውን በፍጥነት ስራ በማስጀመር ለአካባቢው ህዝብ ሰላም፣ልማትና አብሮነት ይሰራል ብለዋል።

ፍቃዱ ከተሰጠን የሰው ሃይልና ቁሳቁስ በማሟላት የመማር ማስተማር ሂደቱን ውጤታማ ከማድረግ ባለፈ የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚያጠናክሩ ስራዎች ይሰራሉም ብለዋል።

በተለይ የወሎን የአብሮነት፣የፍቅር፣ የመቻቻልና የሰላም ተምሳሌት ለትውልድ ለማስተላለፍና ለሌሎች ተሞክሮ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እንሰራለን ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር አቶ እንግዳወርቅ ታደሰ በበኩላቸው አጠቃላይ ሂደቱን በአንድ ዓመት ውስጥ አጠናቀን ስርጭት ለመጀመር በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

ጣቢያው በዩኒቨርሲቲውና በዙሪያው ያሉ የጋዜጠኝነትና ተዘማጅ ትምህርት ተማሪዎችም የሚለማመዱበትና ራሳቸውን የሚያበቁበት ጭምር ይሆናልም ብለዋል፡፡

‘’ሬዲዮ ጣቢያው ስራ ጀምሮ ለአካባቢው ህዝብ ተጠቃሚነት እንዲሰራ የበኩላችንን ጥረት ለማድረግ ዝግጁ ነን’’ ያሉት ደግሞ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ተወካይ ወይዘሮ አባይ ፍስሃ ናቸው፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አቀፍ ሬዲዮ ጣቢያ የተመሰረተ ሲሆን በምስረታውም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም