በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ሴቶች የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ተደረገ

102

ፍቼ ሰኔ 12/2014/ኢዜኣ/ .... በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በፀጥታ ችግር ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ሴቶች የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ተደረገ፡፡

ድጋፉን ያደረጉት የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን እና የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን ከዞኑ ሴቶች ማህበር ጋር በመተባበር ነው።

ፌዴሬሽኖቹን በመወከል ድጋፉን የሰጡት የዞኑ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበርና የድጋፍና ሃብት አሳባሳቢ ኮሚቴ  ሰብሳቢ ወይዘሮ ይርገዱ አያሌው እንዳሉት ድጋፉ  1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ፤ የአልባሳትና የመጠለያ ቁሳቁሶች ናቸው።

ከተለያዩ አካላትና ነዋሪዎች የተሰበሰበው ይኸው ድጋፍ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ 150 እማወራ ሴቶች ጊዜያዊ ችግራቸውን ለማቃለል ታልሞ የተደረገ መሆኑንም ሰብሳቢዋ ገልፀዋል፡፡

ድጋፉ ከግራር ጃርሶ በተጨማሪ በወረ ጃርሶ፤ ደገምና ኩዩ ወረዳዎች ተፈናቅለው ላሉ ሴቶች የሚታደል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በሰነ-ስርኣቱ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ክፈለው አደሬ ህብረተሰቡ በቆየ እሴቱ በመታገዝ ያደረገው ትብብር ስለሆነ ለሌሎችም መልካም አርኣያና ሊከተሉት የሚገባው ነው ብለዋል።

ጊዜያዊ ችግሮችን ለመቋቋም መተባበርና መተጋገዝ ዋና መፍትሄ መሆኑን አመልክተው ሴቶች በሁሉም ዘርፍ የሚያደርጉትን ጥረት ዘላቂ ሰላም በአካባቢው ለማስፈንም እንዲሰሩ ተናግረዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው ሴቶች መካከል ከግራር ጃርሶ ወረዳ ተፈናቅለው የመጡት የሶስት ልጆች እናት ወይዘሮ የውብዳር አሰፋ የተደረገላቸው የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ችግራቸውን በጊዜያዊነት የሚያቃልል በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላው አስተያየት የሰጡት የዚሁ ወረዳ ተፈናቃይ ወይዘሮ ሽቱ አብደታ ህብረተሰቡ ችግራቸውን እንደራሱ በመቁጠር ባደረገው እርዳታ መደሰታቸውን ጠቁመው መንግስት እንዲያቋቁማቸው  ጠይቀዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በፀጥታና በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ  ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ኮሚቴ ተዋቅሮ  እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት የዞኑ አደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቂናጢ ጫላ ናቸው ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም