ዩኒቨርሲቲዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብ እህል ድጋፍ አደረጉ

132

ሰቆጣ ኢዜአ ሰኔ 12/2014 ዓ/ም… የመቅደላ አምባና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች በአሸባሪው ህውሓት ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች 770 ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ አደረጉ።

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የለውጥና የመልካም አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ወንደወሰን ይመር ዛሬ በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ እንዳሉት የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ከወር ደመወዛቸው በማዋጣት የተፈናቀሉ ወገኖች እያገዙ ነው።


በዚህም ከዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች 5ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል።


ዩኒቨርሲቲው ዛሬ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ያደረገው ድጋፍ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የሚገመት 420 ኩንታል የምግብ እህል መሆኑን ተናግረዋል።


ከተደረገው ድጋፍ ውስጥም 200 ኩንታል አልሚ ምግብ ሲሆን፤ 220 ኩንታሉ ደግሞ የዳቦ ዱቄት መሆኑን ገልፀዋል።


የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚያደርጉትን ሰብዓዊ ድጋፍም ችግሩ እስኪፈታ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ ወንደወሰን ጠቁመዋል።


የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ቡድን መሪ ወይዘሮ ዝናሽ ወርቁ ድጋፉ የተፈናቃይ ወገኖችን ወቅታዊ ችግር ለማቃለል ያግዛል ብለዋል።


ዩኒቨርሲቲው ለተፈናቀሉ ወገኖች ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

በተመሳሳይ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከአላማጣና ዙሪያ ወረዳዎች በአሸባሪው የህወሓት ለተፈናቀሉ ወገኖች ወደ 2 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ግምት ያለው 350 ኩንታል የዳቦ ዱቄት ትናንት ድጋፍ አደርጓል።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃን አስማሜ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ምንም እንኳ እንደ አዲስ ራሱን እያደራጀ ቢሆንም ካለው ወገናዊ አስተሳሰብ በመነሳት በጃራ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል።

የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፋሲል አረጋ እንዳሉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ለራሱ በችግር ላይ ሆኖ ሰብዓዊ ድጋፍን በማስቀደም ያደረገው ድጋፍ ለሌሎች አራዓያ የሚሆን ተግባር ነው።

በጃራ መጠለያ ጣቢያ በችግር ላይ ያሉ ከ30 ሺ በላይ ተፈናቃይ ወገኖች የሚገኙ ሲሆን እንደ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ ሌሎች የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ከ86 ሺህ በላይ ተፈናቃይወገኖች በጣቢያዎች እንደሚገኙ ከዞኑ ምግብ ዋስትናና አደጋ መከላከል ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።